Ethiopian National Intelligence and Security Service (NISS)

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

የዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች እጅ አለበት

ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 10, 2020)፦ ከሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ጋር ተያይዞ እስካሁን በይፋ ከተገለጹት መረጃዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በሁለት ኮንቴይነሮች የተሞላ የጦር መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪ ቡድን በኩል ነው።

ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን እንዲገባ የተደረገው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሣሪያ መነሻው ቱርክ መኾኑንም መግለጫው አመልክቷል።

ከቱርክ ሜርሲን ወደብ የተነሳው ይህ የጦር መሣሪያ፤ በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ገብቶ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት፤ በጀቡቲ ወደብ ለአምስት ወሮች በድብቅ ተቀምጦ እንደነበር መግለጫው ያመለክታል። በረቀቀ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የጦር መሣሪያ ግምታቸው ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የኾኑ 501 እሽግ ካርቶኖችና ከ18 ሺህ በላይ ቱርክ ሠራሽ ሽጉጦችን ያካተተ ነው። ለማስመሰያ በኮንቴይነሮቹ ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች የያዙ 229 ካርቶኖችም ተይዘዋል።

የጦር መሣሪያውን ለማሠራጨት የተዘጋጁ 24 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል

የጦር መሣሪያውን በተመለከተ ጥቆማው ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ክትትል በማድረግ ልዩ ኦፕሬሽን ሥራ በመሥራት፤ መሣሪያው በአገር ውስጥ ተሠራጭቶ ጉዳት ሳያደርስ በፊት መያዝ ተችሏል።

በሁለት ኮንቴይነር ውስጥ የተገኘው የጦር መሣሪያ ቢሠራጭ ኖሮ፤ በሕዝብ ደኅንነት ላይ አደጋና ሥጋት ይደቅን እንደነበርም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዛሬ በሠጠው መግለጫ ውስጥ ጠቅሷል።

የጦር መሣሪያዎቹን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማሠራጨት የተዘጋጁ 24 ሰዎች ተጠርጣሪዎች የጦር መሣሪያውን ለመረከብ ሲዘጋጁ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

ከውጭ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች አሉ

የጦር መሣሪያውን ወደ አገር ውስጥ ያስገቡና ያልተያዙ ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎችንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትልና ቁጥጥሩ ይቀጥላል ተብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰባት አገራት ዜግነት ያላቸው የውጭ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ ታውቋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ከሱዳን መንግሥት የመረጃ ተቋም ጋር በተደረገ የጋራ ሥራ ሁለት የሱዳን ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከጂቡቲ፣ ከቱርክ፣ ከሱዳን፣ ከሊቢያና ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ መገኘቱ ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ