የኮሮና ቫይረስ የዓለም ወረርሽኝ ተብሎ ታወጀ
ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም (በቀኝ)፣ በግራ በኩል ያለው ምስል ኮሮና ቫይረስን በምስል ለማሳየት በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የተሠራጨ
የኮሮና ቫይረስ የተከሰተባቸው አገሮች ቁጥር 114 ደርሷል
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 11, 2020)፦ በርካቶች የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተብሎ እንዲፈረጅ ተደጋጋሚ ውትወታ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን፤ ይህንን ለማለት ጊዜው ገና መኾኑን ሲያሳውቅ የነበረው የዓለም የጤና ድርጅት፤ ዛሬ የኮሮና ቫይረስ የዓለም ወረርሽኝ ኾኖ እንዲፈረጅ መወሰኑን አስታወቀ።
ይህንንም ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም ዛሬ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻውን ይፋ አድርገዋል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከቻይና ውጭ በመላው ዓለም የቫይረሱ በፍጥነት መዛመትና በቫይረሱ ተጠቅተው እየሞቱ ያሉ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው። እስካሁን ድረስ ኮሮና ቫይረስ በ114 አገሮች የተዛመተ ሲሆን፤ ከ4100 በላይ ሰዎች በዚህ ቫይረስ ሞተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከ118 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።
ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ አለበት ተብሏል። የኮሮና ቫይረሱ ስም መጠሪያ ኮቪድ-19 (COVID-19) መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)



