Tigray TV, DW and OMN

ትግራይ ቲቪ፣ ድምፂ ወያኔ እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN)

የሣተላይት ሥርጭታቸው የሚከፈለው ከሕዝብ ገንዘብ ነበር

ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. July 6, 2020)፦ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰው ኹከትና የበርካቶችን ሕይወት ካጠፋው ጉዳይ ጋር ተያይዞ የትግራይ ቲቪ እና ድምፂ ወያኔ ከሳተላይት እንዲወርዱ መንግሥት ማድረጉ ታወቀ። በአገር ቤት ሥርጭታቸውን ለማቆም ተገድደዋል።

እነዚህ ሁለት የመገናኛ ብዙኀን በቅርቡ በተከፈተና “ቻናል 29” በሚባል የቴሌቭዥን ሥርጭት በቅርቡ እንደሚያስተላልፉ ማስታወቂያ ሲያስነግሩ እንደነበር ታውቋል። ሁለቱ የመገናኛ ብዙኀን እስከታገዱበት ጊዜ ድረስ ሥርጭታቸውን ሲያስተላልፉ የነበሩት መንግሥት በሚከፍለውና ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ቀረጥ ላይ ከሚወጫ ወጪ መኾኑን ለመረዳት ተችሏል።

ትግራይ ቲቪ እና ድምፂ ወያኔን በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚያስተዳድረውና የሚመራው ሕወሓት እንደኾነ ይታወቃል።

ከሰሞኑ ኹከት ጋር በተያያዘ በአቶ ጃዋር መሐመድ እንደተመሠረተ የሚታወቀው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ከኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሥርጭቱን በመንግሥትና በጸጥታ ኃይሎች እንዲያቋርጥ መደረጉን መዘገባችን አይዘነጋም። በአሁኑ ወቅት OMN ከአሜሪካን ሥርጭቱን እንደቀጠለ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለOMN የሣተላይት ሥርጭት አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት ሥርጭቱን እንዲሰርዝ ለማድረግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ ያስረዳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ