የኦነግ አጋጅና ታጋጅ ድራማ

አጋጁ አቶ ዳውድ ኢብሳ (በቀኝ)፤ ቀሪዎቹ ሦስቱ ታጋጆቹ (በግራ)
ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ስድስት አመራሮች አግጃለሁ ሲሉ፤ ታጋቾቹ የምናውቀው ነገር የለም አሉ
ኢዛ (ረቡዕ ነኀሴ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 12, 2020)፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦነግ ውስጥ መከፋፈል እየታየ ስለመኾኑ በተደጋጋሚ እየተነገር ሲሆን፤ ዛሬ የወጡ መረጃዎች ደግሞ ይህንኑ ክፍፍል አጉልተው ያሳዩ ኾነዋል።
ዛሬ ረቡዕ ነኀሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ከወጡት መረጃዎች መገንዘብ የሚቻለው፤ በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን ስድስት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችን ማገዱን ማሳወቁን ነው።
በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን አገዳቸው ከተባሉት ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች መካከል ከድርጅቱ ሊቀመንበር እውቅና ውጭ ባለፈው ሰኞ ነኀሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ አመራሮች መኾናቸው ታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሳ ቢቂላ፣ የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ ቶሌራ አድባ ይገኙበታል።
በአቶ ዳውድ ይመራል የተባለው ቡድን ያሳለፈው የእገዳ ውሳኔን በተመለከት፤ አቶ ቀጄላ “አጋጅም ታጋጅም የለም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተጠቁሟል። በሌላ በኩልም አቶ ቀጄላ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር ስላለመኖሩም ጠቅሰዋል።
አቶ ቀጄላ የተገኙበት የሰሞኑ የኦነግ መግለጫን በተመለከተ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ማሳወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም እርሳቸው በሌሉበት ተደረገ የተባለው ስብሰባ በኦነግ ውስጥ ክፍፍል አለ የሚለውን አመለካከት እንዲጎላ አድርጎታል። (ኢዛ)