የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የህዳሴ ግድብን በመጎብኘት የመጀመሪያዊ መሪ ሊኾኑ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (በግራ)፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ (በቀኝ)
ጉብኝቱ ሱዳን ከኢትዮጵያ ወገን ስለመቆምዋ የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል
ኢዛ (ረቡዕ ነኀሴ ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 26, 2020)፦ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለመጎብኘት የመጀመሪያው የተፋሰሱ አገር መሪ ሊኾኑ ነው።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያዝ ለቀቅ የሚል አቋም ይዛለች በሚል ስሟ የሚነሳው ሱዳን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ ሐሳብ ያደላ አመለካከት እየያዘች መምጣትዋ ይነገራል።
ይሁንና የሱዳንኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የህዳሴውን ግድብ ለመጎብኘት ፕሮግራም የተያዘላቸው መኾኑ ደግሞ፤ ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ወገን ስለመቆምዋ የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል። በዓባይና በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ዋነኛ ተደራዳሪ ከኾኑት ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በኩል እየተደረገ ያለው ድርድር ይኼ ነው የሚባል መቋጫ ባይገኝለትም፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ጉባ በመጓዝ ግድቡን ይጎበኛሉ መባሉ አንድ እመርታ የሚወስድ ስለመኾኑም እየተጠቀሰ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመጎብኘት ይሁንታ የተገኘው፤ ትናንት ማክሰኞ ነኀሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።
የዶ/ር ዐቢይን የሱዳን ጉብኝት አስመልክቶ ከተሰራጨው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መኾኑንና በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከያዙት ፕሮግራሞቻቸው አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መጎብኘት ነው።
በትናንቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን ጉብኝት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና በአገራቱ መካከል አሉ የሚባሉ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እድል የሰጠ ነው ተብሏል።
ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ መሪዎች መካከል በርካታ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፤ በተለይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ አሉ የሚባሉ ልዩነቶችን ሁሉ በውይይት ለመፍታት የሚቻልበት ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው ተነግሯል።
በተለይ በአፍሪካ ሕብረት መሪዎች አደራዳሪነት የሚደረገው ድርድር ውጤት እንዲያመጣ አገሪቱ በቁርጠኝነት ለመሥራት ተስማምተዋል። ሁለቱ አገሮች (ኢትዮጵያና ሱዳን) በጋራ የሚሠሯቸው በርካታ ነገሮች ያሉ በመኾኑ፤ ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል ተገቢነት ላይም መሪዎቹ እንደተስማሙ ተጠቅሷል። (ኢዛ)



