Prof. Berhanu Nega and Takele Uma

የኢዜማ መሪ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ

213,000 ካሬ ሜትር መሬት በሕገወጥ መንገድ ታድሏል
95 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ላልቆጠቡ ሰዎች ተሰጥቷል
የዚህ ወንጀል ተባባሪዎች ለፍርድ ይቅረቡ ብሏል

ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 31, 2020)፦ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከ213,000 ካሬ ሜትር በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ መታደሉንና 95 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ ለማይመለከታቸውና ለጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ላልቆጠቡ ሰዎች መተላለፉን የሚያመለክተውን በጥናት ላይ የተደገፈ ሪፖርቱን ዛሬ ሰኞ ነኀሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። ጥናቱ የተጠናው በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት አሥር ክፍለ ከተሞች ውስጥ በአምስቱ ክፍለ ከተሞች በተመረጡ 25 ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። በዚህ ወንጀል እጃቸው ያለበት ባለሥልጣናት ለፍርድ ይቅረቡ ብሏል።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ እያለ በጸጥታ ኃይል የታገደበት ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ)፤ ዛሬም በጸጥታ ኃይሎች መግለጫውን እንዳይሰጥ የተከለከለ ሲሆን፤ የዛሬውን መግለጫ በጽሕፈት ቤቱ ለመስጠት ተገድዷል። ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላና ባልተገባ መልኩ ስለተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስመልክቶ ሲያስጠና የነበረውን መረጃና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሕገወጥ ተግባራትን በዝርዝር አቅርቧል።

ኢዜማ በ13 ገፆች የሰነደውና በጥናት ደርሼበታለሁ ባለው በዚህ መረጃ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልጽ የኾነ የመሬት ወረራና ሕገወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ተደርጓል በማለት ገልጿል።

የመሬት ወረራው ከዚህ ቀደም የነበረ እንደነበር የሚያስታውሰው የኢዜማ መረጃ፤ በአዲስ አበባ ግን እንዲህ ባለ ፍጥነትና ስፋት የተስፋፋበት ጊዜ እንዳልነበር በመግለጽ፤ ድርጊቱ እጅግ አደገኛ ስለመኾኑም ሳይጠቅስ አላለፈም።

ወረራውም በተቀናጀ ሁኔታ የተካሔደ እንደነበርም በማውጣት፤ ይህ በጠራራ ፀሐይ በተደራጀ መልኩ የተፈጸመው የመሬት ወረራ፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትሕ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህ አካላት የጉዳዩ ተዋንያን እንደነበሩም ኢዜማ በዚሁ መረጃው ላይ በግልጽ አስታውቋል።

ከጋራ የመኖሪያ ቤቶች እደላ ጋር በተያያዘም የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕገወጥ ተግባር ስለመፈጸሙ፤ ላልቆጠቡ ሰዎች መኖሪያ ቤቶቹ እንዲተላለፉ መደረጉና በሕገወጥ መንገድ ቤቱ እንዲተላለፍላቸው የተደረጉ ሰዎች ከተለያዩ ቀበሌዎች መታወቂያ እንዲሰጣቸው ተደርጐ ጭምር እንደኾነም እማኞችን በመጥቀስ አትቷል።

ከኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ሌላ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች፣ ልጅ የልጅ ልጅ በማለት ለተመዘገቡ ግለሰቦች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሥር ያሉ የንግድ ቤቶች እንደተሰጣቸውም ጭምር አመልክቷል።

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ብዙ መዘዝ ይኖረዋል ያለው የአዲስ አበባ ሕገወጥ የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ውስጥ እጃቸው ያለበት በሕግ እንዲጠየቁ ጭምር አመልክቷል።

ያለአግባብ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው እንዲህ ባለው ወንጀል እጃቸው ያለባቸው ባለሥልጣናት ከቦታው ገሸሽ ማድረግ እና ወደ ሌላ ኃላፊነት ላይ እንዲቀመጡ ማድረግ ሳይኾን፤ ለፈጸሙት ወንጀል በሕግ አግባብ ሊጠየቁ እንደሚገባም አመልክቷል። የኢዜማ ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው(ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ