Gen. Berhanu Julla and PM Abiy Ahmed

ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ (ግራ) እና ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (ቀኝ)

“የትግራይ ሕዝብ ከጁንታው ጋር ያለመኾኑን አስመስክሯል” ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ኢዛ (ቅዳሜ ኅዳር ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 28, 2020)፦ የመከላከያ ሠራዊቱ መቀሌን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ተገለጸ። ጠቅላይ ሚስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ሕዝብ ከስግብግቡ ጁንታ ጋር አለመኾኑን በተግባር ማስመስከሩንና በዚህ ዘመቻ ንጹኀን ዜጎች ዒላማ ሳይኾኑ ከተሞችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት መቻሉንም አስታወቁ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የኾኑት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ ማምሻውን እንዳስታወቁት፤ መከላከያ ሠራዊቱ የመቀሌን ከተማ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኤታማዦር ሹሙን መረጃዎች ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የትግራይ ሕዝብ ከስግብግቡ ጁንታ ጋር እንዳልኾነ በተግባር አስመስክሯል

የመከላከያ ሠራዊት በድል በገሰገሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለአገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር አሳይቷል። ጁንታው ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቀሌ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ አድርጓል። ይህም የሠራዊቱን ድልና የጁንታውን ሽንፈት አፋጥኖታል።

ስግብግቡ ጁንታ በየትኛውም መመዘኛ ለትግራይ ሕዝብ አይመጥነውም። የትግራይ ሕዝብ ከእውነት ጋር በመቆምና የጁንታውን እኩይ ዓላማ በመጻረር ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከዞን ዞን መቀሌ እስኪገባ ድረስ ተመሳሳይ ድጋፍ ለሠራዊቱ ሰጥቷል። ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ጁንታው በሸሸበት ከተማና አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን፣ ት/ቤቶችን፣ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እያወደመ ሔዷል። በዚህም የገዛ ወገኑ ጠላት መኾኑን አሳይቷል። ጁንታው እኔ ከሞትኩ ብሎ ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ።

በዚህ ዘመቻችን ንጹኀን ዜጎች ዒላማ ሳይኾኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ