PM Abiy Ahmed speaks during a question and answer session with Parliament members in Addis Ababa, Ethiopia, November 30, 2020

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም.

ሕወሓት ዶ/ር ዐቢይ ጠ/ሚኒስትር ከኾኑ በኋላ ወደ ቢሮም ኾነ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዳይገቡ ይከለክላቸው እንደነበር ይፋ አደረጉ

ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 30, 2020)፦ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነው ከተሾሙ ዕለት ጀምሮ በሕወሓት ቡድን በተለያዩ ክልከላዎች ሲያደረግባቸው እንደነበርና፣ ወደ ቢሮና ወደ ቤት እንዳይገቡ ክልከላ ሲፈጽምባቸው የነበረ መኾኑን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በፓርላማ ቀርበው እስከዛሬ ያልተነገሩ ምስጢሮችን ጭምር ይፋ ባደረጉበትና “የተለየ” በሚባል ማብራሪያቸው፤ የሕወሓት ቡድን እስከዛሬ በእርሳቸውና በአገር ደረጃ ሲፈጽማቸው የነበሩ ምስጢሮችን ጭምር ገልጸዋል።

ወደ ሥልጣን ከመጡበት ቀን ጀምሮ የነበረው ክልከላ በሌላ አንጻር ለውጡን ለማካሔድ ይጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ አዳጋች እና እጅግ አደገኛ በኾነ ሁኔታ ውስጥ ኾነው ዛሬ ላይ እንዴት እንደደርሱ አብራርተዋል።

በተለይ የተሰጣቸውን አገር የመምራት ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ቢሮ እና ወደ መኖሪያ ቤት እንዳይገቡ የሕወሓት ቡድን ይከለክላቸው እንደነበር ጭምር በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው ተናግረዋል።

እሳቸው ወደ ኃላፊነት በመጡበት ወቅት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ የሕወሓት ቡድን በተለይ ደኅንነቱ ሲፍጥርባቸው የነበረውን ጫና የተለያዩ አስረጅዎችን በመጥቀስ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከሕዝብ ይቀርብ የነበረውን የለውጥ ጥያቄ በአግባቡ ለመምራት እንኳን እጅግ ፈተና እንደነበር የሚያመለክቱ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ጭምር እስከ ዛሬ ያልተሰሙ ድርጊቶችን ይፋ አድርገዋል።

እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን ከመቆጣጠር ባለፈ፤ የግል ጠባቂዎቻቸውን እንኳን ለመቀየር እንዳይችሉ በማድረግ፤ በወቅቱ በነበረ የደኅንነት ኃላፊ ሲፈጸም የነበረውን የማይገመት ድርጊት በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ በዝርዝር በማቅረብ፤ የሕወሓት ቡድን ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ሲፈጽም የነበረውን ደባ ፓርላማውና ሕዝብ ያውቅ ዘንድ አካፍለዋል።

የለውጡን ሒደትና ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የሕወሓት ቡድን ምን ሲያደርግ እንደነበር ወደኋላ መለስ ብለው አጠቅላይ ስዕሉንና አሁን የተደረሰበትን ደረጃ በቁጭት ጭምር ማብራሪያ በሰጡበት በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውንና በተለይ በወታደራዊና በደኅንነት ዘርፉ ላይ የነበረውን ቁልፍ ሚናን በአጭር ጊዜ ለማስተካከል ከባድ እንደነበርም አመልክተዋል።

በወቅቱ ዛሬ ይህንን ሥር የሰደደ ኃይል በለውጡ ማግስት እርምጃ ለምን አይወሰድበትም ነበር የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት ሲቀርቡ የነበረ ሲኾን፤ በዚያን ወቅት እርምጃ መውሰድ ሊያስከትል የነበረውን ጥፋት ከግምት በማስገባት፤ በዘዴና በጥበብ እያስተካከሉ ዛሬ ላይ መደረሱንም አብራርተዋል።

በተለይ በመከላከያ ውስጥ የሕወሓት ቡድን ምን ያህል እንደተንሰራፋና መከላከያው በሕወሓት አባላት አመራር ሥር እንደነበር በማብራራትም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ የአንድ ብሔር አመራር በምን ያህል ደረጃ እንደነበርም በአኀዝ ጭምር አስቀምጠዋል። ከዚህ አንጻር ከገለጹት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

- ባለ አራት ኮኮብ ጄኔራል 60 በመቶው ከአንድ ቡድን ነበር፣ ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ደግሞ የነበረው ስብጥር 40 በመቶ ብቻ
- ሌተናንት ጄኔራል 50 በመቶ ከአንድ ቡድን
- ሜጀር ጄኔራል 45 በመቶ ከአንድ አካባቢ
- ብርጋዴር ጄኔራል 40 በመቶ ከአንድ አካባቢ
- ኮሌኔል 58 በመቶ ከአንድ አካባቢ
- ሌተናል ኮሎኔል 66 በመቶው ከአንድ አካባቢ
- ሻለቃ 53 በመቶ ከአንድ አካባቢ
- በጥቅሉ ከጄኔራል እስከ ሻለቃ ድረስ በአማካይ ሲታይ 55 በመቶው ከአንድ ክልል ብቻ ነበር ስብጥሩ
- ኢትዮጵያ በነበሯት ሁሉም ዕዞች ይመሩ የነበሩት ዋና እና ምክትል ከአንድ ቡድን ወገን ነበሩ
- ከዚህ በተለየ በሰሜን ዕዝ ላይ ዋና እና ምክትል አዛዥ፣ ሎጂስቲክ፣ አስተዳደርን የሚመሩት ሁሉም ከሕወሓት ቡድን ነበር
- ከዕዝ በመለስ የመካናይዝድ ክፍለ ጦሮችን በሙሉ 100 በመቶ እና የእግረኛ ክፍለ ጦሮችን 80 በመቶ የሚመሩት በዚሁ በአንድ ቡድን ነበር
- ከወታደራዊ መለዮ ለባሾች ባሻገር የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት 80 በመቶው ተይዞ የነበረው በአንድ ቡድን ነበር” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

የዛሬውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በተለይ ያደመጠውና የተመለከተው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የለውጡ ኃይል በምን ያህል ፈተና ውስጥ ቆይቶ ዛሬ ላይ እንደደረሰ ብዙ ግንዛቤ ያገኘበት ስለመኾኑ በተለያየ መንገድ የተገለጸበት ሲሆን፤ በተለይ ከትግራይ ሕግ ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ የተገኘው ድል ታሪክ ሊያስታውሰው የሚችል ትልቅ ክንውን ስለመኾኑ ገልጸዋል። ለዚህ ጦርነት የተደረሰበትን ምክንያትና በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን የአገር ክህደትም እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ የገለጹበት ነው።

የሰሜን ዕዝ አዛዥን በምግብ በመመረዝ ጭምር በሕወሓት የተፈጸመውን ድርጊት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕግ ማስከበር ሥራው ከተጀመረ በኋላ ደግሞ በቀናት ዝግጅት የተገኘውን ድልም በዝርዝር አቅርበዋል።

በአብዛኛው እስከዛሬ ያልተነገሩና አዳዲስ መረጃዎችን ላካተተው የዛሬው ማብራሪያቸው ከሕወሓት ጁንታ ቡድን ጋር በተደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ በተለየ ከሚታይባቸውና ሊጠቀስ ከሚችለው ውስጥ፤ በዚህ ጦርነት እስካሁን ሰላማዊ ሰው ያለመሞቱንና ሰላማዊ ሰዎች እንዳይሞቱ ዘመቻው በጥንቃቄ መካሔዱን ጭምር ነው። ይህ የዘመቻ ስትራቴጂ ያስገኘው ውጤትም በተመስጦ ሲያደምጧቸው የነበሩ የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ጭምር እንዲያጅቡት ያደረገ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ የፓርላማ ውሎ የሚያሳየውን ቪዲዮ የማጫወቻ ቁልፉን በመጫን ይመልከቱ! (ኢዛ)

ክፍል አንድ

 

ክፍል ሁለት

 

ክፍል ሦስት

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!