ከ34 ዓመታት በላይ ጊዜ የወሰደው የንግድ ሕግ ማሻሻያ ጸደቀ
መርካቶ
በ825 አንቀጾቹ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 25, 2021)፦ ከ60 ዓመት በላይ ሲያገለግል የቆየው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፤ ዛሬ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ።
ከ34 ዓመታት በላይ ይህንን ሕግ ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉበት የነበረ ሲሆን፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቁ ቀርቦ ሊጸድቅ ችሏል።
825 አንቀጾች ማሻሻያ የተደረጉበት ይህ ሕግ፤ አሁናዊ የዓለም እና አገራዊ የንግድ አሠራሮችን ከግምት በማስገባት የተሰናዳ ነው።
አዳዲስ አሠራሮችን እና ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰሩ ድንጋጌዎችንም እንዲያካትት የተደረገው ይህ የተሻሻለው የንግድ ሕግ፤ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት ለመግባት እንቅፋት ኾኖባታል የተባሉ አንቀጾችም ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።
በተለይ ወደ ንግድ ውስጥ ለመግባት የተንዛዛ አሠራርን ሊያሳጥሩ የሚችሉ አንቀጾችን እንዲይዝ ተደርጓል።
በተሻሻለው የንግድ ሕግ ከተካተቱት አዳዲስ አንቀጾች ውስጥ የአክስዮን ኩባንያዎች እና የንግድ ተቋማት ጠቅላላ ጉባዔአቸውን በኦንላይን (በበይነመረብ) ማድረግ የሚችሉ መኾኑን ነው።
የዚህ አንቀጽ መካተት፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ትላልቅ የአባላት ቁጥር ያላቸው የአክስዮን ማኅበራትን ይጠቅማል ተብሎ የሚታሰብ ነው።
ዜጎች በማንኛውም የንግድ ሥራዎች ውስጥ እንዲሰማሩ የሚያስችል ድንጋጌ ያለው ሲሆን፤ እስካሁን በግለሰብ ደረጃ አክስዮን ኩባንያ ለመመሥረት የማይቻል ሲሆን፤ በዚህ የተሻሻለው ሕግ ግን፤ አንድ ግለሰብ የአክስዮን ኩባንያ እና የንግድ የሕብረት ሥራ ማኅበር መመሥረት ይችላል።
በአጠቃላይ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ያቀላጥፋል፣ ከዓለም አቀፍ የንግድ አሠራሮች ጋር ይስማማል የተባለው ይህ ሕግ፤ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በሙሉ ድምፅ ጸድቋል። (ኢዛ)



