የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ባንኩን ችግር ውስጥ ከከተቱት በርካታ ምክንያቶች መካከል ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች በገፍ የተሰጠው ብድር አንዱ

ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 8, 2021)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ አሴት አላቸው ተብለው ከሚጠቀሱት መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅተ ወደ አንድ ትሪሊዮን የሚጠጋ (938 ቢሊዮን ብር) አሴት ያለው ሲሆን፤ የአገሪቱ ትልቁ ባንክም ነው። ከባንክ ኢንዱስትሪው ወደ 65 በመቶ የሚኾነውን የገበያ ድርሻ የያዘም ነው። ይህ አንጋፋ ባንክ ሰማኒያኛ ዓመቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ ያለ ሲሆን፤ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ሲሰጥ የነበው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው። እንደ ፖሊሲ ባንክ የሚታይ ነው።

ባንኩ ከአገሪቱ ባንኮች በተለየ የሚታይባቸው ሌሎች መገለጫዎች ያሉት በመኾኑ ሲሆን፣ የዚህ ባንክ ሕልውና ወሳኝ ነው።

ይህ ሰማኒያ ዓመታትን የተጓዘ ባንክ ግን ከለውጡ ቀደም ብሎ በነበሩ ዓመታት የተዘፈቀበት ችግር ግን አሁን ላይ እየተገለጠ ሲመጣ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር መገንዘብ ተችሏል።

ሰሞኑን ባንኩ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ሪፖርቱን ሲያቀርብ በቦታው ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አትናፉ (የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩ) እንዳመለከቱት ባንኩ በከፋ ችግር ውስጥ እንደነበር፤ እንደውም መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር ነው።

በራሳቸው ገለጻ ባንኩን ችግር ውስጥ ከከተቱት በርካታ ምክንያቶች መካከል ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች በገፍ የተሰጠው ብድር አንዱ ነው።

ይህ ብድር ወደ 700 ቢሊዮን ብር የሚኾን ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ይህንን ገንዘብ ለመክፈል የሚችሉበት እድል አለመኖሩ ባንኩ ከማይወጣው ችግር ውስጥ አስገብቶት ቆይቷል።

ይህንን ያህል ብድር ያለባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አሁንም ብድሩን ለመክፈል የማይችሉ መኾኑ መታወቁ ደግሞ ባንኩን አጣብቂኝ ውስጥ ሊከተው ችሏል።

እንዲያውም ባንኩ የገንዘብ እጥረት እንዲገጥመው በማድረግ ጭምር የፈጠረው ጫና የባንኩን ሕልውና እስከመገዳደር መድረሱንም የአቶ ተክለወልድ ገለጻ ያመለክታል።

ይህ ባንኩን የፊጢኝ የያዘው ችግር ካልተፈታ፤ ባንኩን ማራመድ አይደለም ሥራውን ለማስቀጠል ከባድ በመኾኑ፤ ቦርዱ ለመንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የእነዚህ የልማት ድርጅቶች ብድር ምን እናድርግ በሚል ከተመከረ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነውን የልማት ድርጅቱን ብድር ወደ መንግሥት እንዲዛወር በመወሰናቸው፤ ባንኩ ነፍስ ሊዘራና አሁን እንዲያንሠራራ ኾኗል።

ይህ ባይኾን ኖሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ የሚፈጠረው ቀውስ ለአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚ መንኮታኮት ምክንያት ይኾን ነበር።

አቶ ተክለወልድም እንዳስረዱት ንግድ ባንክ ችግር ባይፈታ ወይም ችግር ባይገጥመው አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማትን ጭምር አደጋ ላይ የሚጥልና የአገር ኢኮኖሚም በእጅጉ የጐዳ ኾኖ ነበር።

ኾኖም ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በባንኩ ውስጥ የተደረገው ሪፎርም የተበላሹ አሠራሮችን እያስተካከለ ለመሔድ መቻሉንም ገልጸዋል።

አሁን በዘጠኝ ወር የባንኩ ከታክስ በፊት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉ የብዙ ለውጦች ውጤት መኾኑን ጠቁመዋል።

በጥቅል ሲታይ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጣዊ አሠራር እጅግ የተበለሻሸ እና ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገሉ መመሪያዎችን ጭምር ይጠቀም የነበረ መኾኑን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፤ አሁንም ባንኩን ለማጥራት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በተለይ የሰው ኃይል የማፍራት ችግር ያለበት መኾኑን የገለጹት አቶ ተክለወልድ፤ ሰው ማፍራት ያልቻለ ጭምር በመኾኑ ባንኩ ከሌላ ባንክ ፕሬዝዳንት ለምኖ ማምጣቱን አመልክተዋል።

ሌላው ያነሱት ነጥብ ባንኩ የአንድ ክልል ምክር ቤት አይደለም። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነውና ስሙን በመጠነ መልኩ ሁሉንም ብሔር ያሰባጠረ የሰው ኃይል ምደባ የሚደረግ መኾኑን ገልጸዋል።

አሁን ይህ እየተሠራበት ሲሆን፣ ከዚህ ጐን ለጐን ባንኩን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከውጭ ኩባንያ ጋር በመኾን ሪፎርም ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

ባንኩ ካለው አቅም አንጻር አሁን እየሠራ ያለው ትንሽ በመኾኑም፤ ገበያውን የማስፋት ትልቅ ሥራ ስለሚጠብቀው ሠራተኞች ለዚህ መዘጋጀት እንዳለባቸው ሳያሳስቡ አላለፉም።

ከ65 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ቀጣዩ የሪፎርም ጉዞው የት ድረስ እንደሚወስደው ባይታወቅም፤ በባንኩ ውስጥ የለውጥ ንቅናቄ እየታየ ነው።

ትልቁ እውነት ግን ያለአግባብ በዘፈቀደ ሲታደል የነበረው ብድርና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ተብለው የተሰጡ ብድሮች፤ ባንኩን መቀመቅ ውስጥ ከተውት የነበረ መኾኑ ነው። መንግሥት ዕዳው ወደ እኔ ይዛወር ባይል፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይኖር ይችል ነበርና፤ ከዚህ በኋላም ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ቆጣቢዎችን የያዘው ይህ ባንክ፤ ከችግሩ ወጥቶ ለመራመድ አሁንም ብርቱ ሥራዎች የሚጠብቁት መኾኑ ነው።

እንደ ብዙዎች እምነት ደግሞ አዋጭ ላልኾኑ ፕሮጀክት ብድር ስጡ የሚለው አሠራር ካልተለወጠ፤ አሁንም ባንኩን መልሶ ችግር ውስጥ እንዳይከት መንግሥት እጁን ሰብሰብ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ምክር እየተሰጠ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ