Ethiopia and Sudan border conflict

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ያለው ፍጥጫ ቀጥሏል

ከሱዳን የተነሱ የሕወሓት ታጣቂዎች ተደመሰሱ
የሱዳን እና የሕወሓት ምስጢራዊ ወታደራዊ ስምምነት ሰነድ ተይዟል

ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 16, 2021)፦ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ግልጽና በስውር ወታደራዊ ዘመቻ ስለመክፈቷ የሚያመላክቱ አስረጅዎች ጐልተው እየወጡ ነው። በተለይ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት እስካሁን የኢትዮጵያ ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ድንበር የመድፈር ሕገወጥ ተግባሯ ባሻገር በተከታታይ እየፈጸመች ያለችው ድርጊት በሁለቱ አገሮች መካከል ውጥረት ፈጥሯል።

ባለፈው ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ ደግሞ ሱዳን ኢትዮጵያን ለማጥቃት ግልጽ የኾነ እቅድ ይዛ ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ከወነጀለቻቸው ቡድኖች ጋር ሳይቀር በጋራ በመኾን እየሠሩ መኾኑ ነው።

የአገር መከላከያ የሚኒስቴር የመከላከያ ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብ/ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለጹት፤ የሱዳን የጦር መኮንኖች ከሕወሓት ጁንታ ቡድን ጋር በትብብር ለመሥራት የተስማሙ ስለመኾኑ የሚያመለክት ምስጢራዊ ሰነድ ተይዟል።

ዓርብ ከሱዳን ሠልጥነው ወደ አገር ሲገቡ ስለተደመሰሱ የጁንታው ታጣቂዎችን አስመልክቶ ጄኔራሉ እንደገለጹት፤ “የጁንታው ኃይል ከጥቂት የሱዳን ጄኔራል መኮንኖች ጋር በመተባበር ድብቅ የጋራ ስምምነት የሚመስል ወታደራዊ የምሲጥር ሰነድ ተይዟል” ብለዋል።

እንዲህ ያለው የሱዳን ድርጊት በሁለት አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ከማሻከሩም በላይ፤ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚለው አመለካከት እያጐላው ነው። ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን ችግር የበለጠ እያወሳሰበችው ስለመኾኑ ሌላው ማሳያ በቅርቡ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን የቤንሻንጉል ክልል የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ መኾኑ ነው።

ይህ አግራሞትን የፈጠረው የሚኒስትሯ ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ድፍረት ቅጥ ያጣ ነው ብሎ ንግግራቸውን በእጅጉ ያወገዘው ቢኾንም፤ ሱዳን ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያስችለኛል ያለቻቸውን ድርጊቶች በገሀድም ኾነ በስውር እየተገበረቻቸው ነው።

በጋምቤላ ክልል ውስጥ እየተፈጠረ ያለውና ለብዙዎች ሕይወት ሞት ምክንያት ለኾኑት ጥቃቶች በስውር እጃቸው አሉባቸው ከሚባሉት ውስጥ የሱዳን ስም መነሳቱም የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች አካሔድ አደገኝነትን ያመለክታል።

የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉት ጥረቶች ሲደማመር ነገሩ በዝምታ ወይም ጊዜ መስጠት የሚያስፈልገው ነው ተብሎ አይታሰብም።

ለዚህም እንደ አስረጂ የሚቀርበው የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮችን አፈናቅሎ ትላልቅ የእርሻ ማሳዎችን ካቃጠለ በኋላ በያዛቸው መሬት ላይ ወታደራዊ ካምፖችን መገንባት መቀጠሉ ነው።

ከሰሞኑም ከወደ ሱዳን የተሰማው ዜና ሱዳን በኃይል በያዘችው መሬት ላይ የድልድዮች ግንባታ እያካሔደች መኾኑ ነው።

አስገራሚው ነገር ይህንን የድልድይ ግንባታ በቦታው ተገኝተው የጐበኙት የሱዳን አንድ ወታደራዊ መኮንን ተናገሩ የተባለው ነው።

ሸምሰዲን ከባሼ የተባሉት እኚህ ጄኔራል፤ እነዚህ ድልድዮች ግንባታቸው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቁ የሚፈለገው በክረምቱ ወቅት የሱዳንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተመቸ እንዲኾን ለማድረግ ነው የሚል አንደምታ ያለው ነው።

ይህ በግልጽ በሱዳን ሚዲያ የተላለፈው ንግግራቸው፤ የሱዳን እርምጃ ኢትዮጵያ እያቀረበች ላለው ሰላማዊ ጥሪ ጆሮ ዳባ ማለቷን ጭምር ነው። የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት ላለመልቀቅ ያላትን ፍላጐት በማረጋገጥ የሰጠችው ምላሽ መኾኑንም የሚያመለክት ነው።

ዓርብ ዕለት ጄኔራል ተስፋዬ ከሰጡት መግለጫ መገንዘብ እንደሚቻለው፤ ሱዳን የሕወሓት ጁንታ ቡድን በብርቱ እየደገፈች መኾኑን ብቻ ሳይኾን፤ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵየ የሚገቡ ታጣቂዎችን እንዲሠለጥኑ በግልጽ መፍቀዷን ነው። እንዲህ ካለው ፍቃድ በላይ ወታደራዊ መሣሪያዎችንም የምታቀርብ መኾኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸው የሱዳን ወታደራዊ መኮንኖች ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት እየገፏት መኾኑን ሊያስገነዝብ ይችላል።

የጁንታው ኃይል አካል የኾነው እና በማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ የሣምሪ ቡድን አባላት ሱዳን ገብተው ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲገቡ የተደረገው በሱዳን ድጋፍ ጭምር መኾኑም ግልጽ ነው።

ጄኔራል ተስፋዬ እንዳመለከቱትም በማይካድራ ጭፍጨፋ በማድረግ ሱዳን ገብተው ከነበሩት ውስጥ የተወሰኑት በሁመራ በኩል ሊገቡ ሲሉ በአገር መከላከያ ኃይል ተደምስሰዋል።

እነዚህ በሱዳን ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው በሁመራ በኩል ሊገቡ ሙከራ ሲያደርጉ የተደረሰባቸው 320 የሚደርሱት የጁንታው አባላት የተለያዩ መድሃኒቶች እና የጦር መሣሪያዎች የያዙ ነበሩ። እነዚህ የጁንታው አባላት ገሚሱ ሲደመሰስ ቀሪዎቹ መያዛቸውም ተገልጿል።

እንደ ጄኔራሉ ገለጻ አሁንም ቀሪ ኃይል ከኋላ አለ ማለታቸው ከሱዳን የሚነሱ መኾኑን የሚያመለክት በመኾኑ፤ የሱዳን ነገር ቅጥ ያጣ ድፍረት ነው ተብሎ የሚታለፍ አለመኾኑን አመላካች ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ