TPLF (The terrorist group)

ሽብርተኛው ሕወሓት

ንፋስ መውጫና በሌሎችም አካባቢዎች የሴቶች ቀለበት፣ የጆሮ ወርቅ ሀብልና የመሳሰሉትን ሳይቀር ዘርፈዋል

ሪፖርታዥ

ኢዛ (ረቡዕ ነኀሴ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. August 25, 2021)፦ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በቅርቡ ይዟቸው የነበሩ የአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት መድረሱ እየተገለጸ ነው። የሽብርተኛው ቡድን በገባባቸው ከተሞች በተለይ የፈጸማቸው ዘረፋዎች ከቤት ቁሳቁስ ጀምሮ እስከ ትላልቅ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ነቅሎ እስከመውሰድ የደረሰ መኾኑን ሰሞኑን በተከታታይ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

ለዘረፋ ተልዕኮ የተሰጣቸው የሽብር ቡድኑ አባላት በደረሱበት አካባቢ ሁሉ ያልዘረፉት የንብረት ዐይነት እንደሌለ ተገልጿል። በእነዚህ በወረራ ተይዘው ከነበሩ ከተሞች አንዷ በኾነችው ወልድያ ከተማ ብቻ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባጃጆች ተዘርፈዋል።

በደረሰባቸው ከተሞች ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል። እንደ ወልደያ ሆስፒታል ያሉ የጤና ተቋማት በእነዚሁ ዘራፊዎች የተዘረፉ ሲሆን፤ ማጓጓዝ ያልቻሉትን ደግሞ አውድመዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ንብረቶች በተመሳሳይ በዘራፊ ቡድኑ ስለመወሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የበርካታ ባለሀብቶች የተለያዩ ንብረቶች የተዘረፉ እና የወደሙ ስለመኾኑም እኒሁ ሰሞናዊ መረጃዎች አመላክተዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ የጥፋት ተልእኮን የበለጠ አስከፊ ያደርጋል ተብሎ ከሚጠቀሱት ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የገበሬዎችን ንብረት ከመዝረፍ ባለፈ፤ ነድቶ መውሰድ ያልቻላቸውን ከብቶች በጥይት እየረፈረፈ አካባቢዎቹን ጥሎ መውጣቱ ነው። በአሁኑ ወቅት የሽብር ቡድኑ በወረራ ከያዛቸው የአማራና የአፋር ክልሎች እየተመታ የወጣና እየወጣ ቢኾንም፤ ጥሎት የሔደው ውድመት ግን ቀላል ያለመኾኑን ለመገንዘብ ተችሏል።

የአሸባሪ ቡድኑ ሰሞናዊ ጥፋት በተመለከተ አስተያየታቸውን ከሰጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ከያዛቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሕዝብን ማውረድና ትግራይን በተዘረፈ ሀብትና ንብረት መገንባት መኾኑን የገለጹት አቶ ገዱ፤ ቡድኑ ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በሰሜን ወሎ ዋግህምራ፣ በደቡብ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም አመልክተዋል።

የሕወሓት ወራሪ ኃይል ወደ አማራ ክልል መግባት ከጀመረበት ጊዜያት ጀምሮ ብዙ ጥፋቶችን መፈጸሙን አቶ ገዱ አመልክተዋል።

ይህንንም ሲያብራሩ “በሰሜን ወሎ በዋግህምራ፣ በሰሜን ጐንደር፣ በደቡብ ጐንደር አካባቢ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔደ የውጭ ወረራ ሕብረተሰብን ለማደህየት፣ አካባቢን ለማራቆት ኾን ተብሎ የተሠራ ሥራ አላነበብኩም። አይቼም አላውቅም” በማለት የተፈጸመውን አስከፊ ጥፋት እስከመግለጽ ደርሰዋል።

እንደ አቶ ገዱ ገለጻ፤ ወራሪ ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች የመንግሥት ተቋማትን ማፈራረሱ፤ ሕብረተሰብ የሚገለገልባቸውን የጤና የትምህርት የግብርና ተቋማትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በሙሉ ይዘርፋቸዋል።

ለዚህ አገላለጻቸው በምሳሌነት የጠቀሱት ደግሞ የቆቦ፣ የወልድያ፣ የኮን መቅዬት፣ የላሊበላ፣ የሰቆጣ፣ ንፋስ መውጫ፣ አደርቃይት፣ መርሣ ከተሞች ሆስፒታሎችን ጣራና ግድግዳቸው ሲቀር ሁሉንም ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን በሙሉ ዘርፈው ወደ ትግራይ ጭነው ወስደዋል።

ከእነዚህ ከተሞች የሆስፒታል ዘረፋውን ብቻ እንደ ምሣሌ አነሱ እንጂ፤ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ያሉ ተቋማትን ንብረት፣ የጤና ጣቢያዎች መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ስለመዘረፋቸው አቶ ገዱ ተናግረዋል።

ዘረፋው በዚህ ብቻ ያበቃ ሳይኾን የቴሌኮምዩኒኬሽን መሠረተ ልማቶችን ከመዝረፍ ባለፈ አበላሻሽተዋል። መውሰድ የሚችሉትን የእነዚህ መሠረተ ልማት ንብረቶች ዘርፈው መውሰዳቸውንም አቶ ገዱ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የሽብር ቡድኑ ሰሞኑን የዘረፋ ዘመቻ በዚህ ብቻ እንዳላበቃ የሚጠቁመው የአቶ ገዱ ማብራሪያ፤ ንፋስ መውጫና በሌሎችም አካባቢዎች የሴቶች ቀለበት፣ የጆሮ ወርቅ ሀብልና የመሳሰሉትን ሳይቀር ዘርፈዋል።

የሕወሓት ዘረፋ ታይቶ የማይታወቅ ስለመኾኑ በቃለ ምልልሳቸው የገለጹት አቶ ገዱ፤ የቡድኑን ዓላማ በተመለከተ ከገለጹት ውስጥ፤ “አሁን የወራሪ ኃይሉ ዓላማው አገራችን ኢትዮጵያን ማፍረስ፣ ሕዝባችንን ማዋረድ፣ ንብረታችንን ዘርፎ በተዘረፈ ሀብትና ንብረት ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ነው” የሚለው ይገኝበታል።

እንዲህ ያለው ዘረፋ በተመሳሳይ በተለያዩ የአፋር አንዳንድ ከተሞች ላይ የተፈጸመ ስለመኾኑ አቶ ገዱ ያስታወሱ ሲሆን፣ ይህንን ግብስብስ ኃይል በመደምሰስ አገራችንን ወደተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ እየታየ ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ሁሉም ሕብረተሰብ ይህንን ኃይል ለመደምሰስ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበትም ያሳሰቡት አቶ ገዱ፤ በተለይ ወጣቱ ሠልጥኖ መዋጋት እንዳለበት አመልክተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ