Merkato, Addis Ababa, Ethiopia

መርካቶ ገበያ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የዋጋ ግሽበት፥ የገንዘብ ለውጥ፣ ያልተጠበቁትና ዱብ ዕዳ የኾኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች

ኢዛ (ዓርብ ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 10, 2021)፦ የ2013 ዓ.ም. ለመጠናቀቅ ሰዓታት ቀርተውታል። ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰዓታት በቀሩት 2013 ዓ.ም. በአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ከተከሰቱ ክንውኖች አንኳር የኾኑት የብር ለውጥ እና አንደምታውም ከዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።

የዋጋ ግሽበቱም ቢኾን የብዙዎችን ኑሮና ጓዳ ያንኳኳ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል በሚል ያወጣቸው አዳዲስ መመሪያዎች ቢኖሩም፤ መመሪያዎቹ የባንኮችን እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጥቅም የሚገድቡ ናቸው ተብለዋል። በ2013 ዓ.ም. አንኳር ናቸው ብለን የመረጥናቸውን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። መልካም ንባብ!

የዋጋ ግሽበትና 2013

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ሲታሰብ ቀድሞ የሚጠቀሰው በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ የተባለ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ ነው። ይህ የዋጋ ግሽበት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረበት በእጥፍ ጨምሮ፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ 30 በመቶ አካባቢ መድረሱ ነው። ይህንን የዋጋ ግሽበት ለማቃለል መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢኾንም፤ አሁንም ግሽበቱን ለመቆጣጠር አዳጋች ኾኗል።

በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ግን መንግሥት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ቀረጥ እንዲነሳ በማድረጉ፤ ይህ ውሳኔው የተወሰነ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ የተገመተ ቢኾንም፤ አሁንም በሁሉም ዐይነት ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎች እየታዩ ነው። ዜጐች በዚህ ረገድ በብርቱ የተፈተኑበት ዓመት ቢኖር 2013 ዓ.ም. ኾኖ ሊያልፍ ነው።

የዋጋ ግሽበቱ ችግር ግን የ2013 ዓ.ም. ተሻግሮ በቀጣይ ዓመትም መሻገሩ የማይቀር መኾኑም እየተነገረ ነው።

በተለይ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው ችግር በአካባቢው እርሻ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ የምርት መጠንን ሊቀንስ መቻሉ የዋጋ ግሽበቱ ቀጣይ ሊኾን ይችላል የሚለው ሥጋት ያጠናክረዋል።

Merkato Market, መርካቶ ገበያ
መርካቶ ገበያ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የገንዘብ ለውጥ

በ2013 ተጠቃሽ ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ውስጥ አንዱ የብር ኖት ለውጥ መደረጉ ነው። ይህ የገንዘብ ለውጥ በሁለት ወር ውስጥ ተጠናቅቆ የተፈጸመ ሲሆን፡ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሚሉ አወንታዊ አሻራዎችን አሳርፎ እንዳለፈ ይታመናል።

የብር ለውጡ የአገሪቱ ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻሉበት ሲሆን፤ በብር ለውጡ ወቅት ብቻ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የባንክ ደንበኞች የቀጠለ ሒሣብ የከፈቱበት ነው። በዓመቱ መጨረሻ እንደተገለጸውም በአገሪቱ ባንኮች የባንክ ቁጠባ ደብተር ያላቸው ከ62 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ይህ ቁጥር አንዳንዶቹ ሁለትና ሦስት የሒሣብ ደብተር ያላቸው ቢኾንም፤ በ2012 ዓ.ም. በባንኮች የቁጠባ ደብተር የከፈቱ ደንበኞች 38 ሚሊዮን የነበረ ከመኾኑ አንጻር በ2013፤ 62 ሚሊዮን መድረሱ ትልቅ ለውጥ ነው ተብሏል።

ያልተጠበቁት እና ዱብ ዕዳ የኾኑት መመሪያዎች

በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ባንኮች ከገንዘብ ለውጡ ጋር ተያይዞ ተጠቃሚዎች የኾኑበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ዓመቱ ከኢኮኖሚ አንጻርም በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ዓመቱን አትራፊ ኾነው አጠናቀዋል። አብዛኛዎቹ ባንኮች ዓመታዊ ትርፋቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ኾኗል።

ወደ ዓመቱ መጠቃለያ ላይ ግን ከብሔራዊ ባንክ የወጡ መመሪያዎች ባንኮችን የሚጐረብጡ ኾነዋል። እነዚህ መመሪያዎች በዋናነት ባንኮች ከሚሰጡት ብድር አምስት በመቶውን በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የ5 በመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ወደ አሥር በመቶ ከፍ ማለቱን የሚያመለክት ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ባንኮች በየዓመቱ ከሚሰጡት ብድር አንድ በመቶውን በማስላት ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድድ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሦስተኛው መመሪያ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ከሚያገኙት ትርፍ 15 በመቶውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድ ግዥ መፈጸም እንዳለባቸው የሚደነግግ ነው።

እነዚህ ሦስት መመሪያዎች የወጡት ከወቅታዊው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ቢኾንም፤ ባንኮችን የሚጫን እንደኾነ እየተገለጸ ነው።

ከእነዚህ መመሪያዎች ሌላ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚገልጸው ሌላው መመሪያ ደግሞ ተሻሽሎ የቀረበ ነው። ከዚህ መመሪያ በፊት ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶን ለብሔራዊ ባንክ በዕለታዊ የምንዛሪ ዋጋ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሲኾን፣ በቅርቡ የወጣው መመሪያ ደግሞ 30 በመቶ የነበረውን ወደ 50 በመቶ አሳድገውባቸዋል።

በእነዚህ መመሪያዎች ዙሪያ እየተሰጠ ያለው አስተያየት የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የባንኮችን ጥቅም የሚገድብ ነው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይቀመጥ የተባለ ገንዘብ በእጥፍ ማደጉ ባንኮች ገንዘቡን አበድረው ተጨማሪ ትርፍ እንዳያገኙ ያደርጋል የተባለ ሲኾን፣ በተለይ በብሔራዊ ባንክ የሚቀመጠው 10 በመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ምንም ወለድ የማይከፈልበት በመኾኑ፤ ባንኮቹ በሰባት በመቶና ከዚያም በላይ ወለድ ከፍለው ያሰባሰቡትን ገንዘብ ጭምር ያለምንም ወለድ በብሔራዊ ባንክ እንዲቀመጥ መደረጉ እንደሚጐዳቸው ያመለክታሉ። የቦንድ ግዥዎቹም ቢኾኑ ባንኮቹ አበድረው ትርፍ ሊያገኙበት የሚችሉበት ቢኾንም፤ በዚህ መንገድ ለቦንድ ግዥ እንዲውል መደረጉ አግባብ አለመኾኑም እየተነገረ ይገኛል።

ከባንኮች ወገን እነዚህ መመሪያዎች ባንኮቹን የሚጐዱ ናቸው ብለው የገለጹት ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገቡ መባላቸውም ትልቁ ችግር፤ ይህንን ውጭ ምንዛሪ ለደንበኞቻቸው በመስጠት ያገኙ የነበረውን ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳሳ ኾኖ መገኘቱ ነው።

የእነዚህን መመሪያዎች ጉዳት ባለሙያዎች በተለያዩ መልኮች እየተነተኑ ቢኾንም፤ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተግባራዊ እንዲኾን ተደርጓል።

መጨረሻ ለባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳም ኾኗል። በብሔራዊ ባንክ በኩል ደግሞ የእነዚህ መመሪያዎች መውጣት ዋነኛ ምክንያት ወቅታዊ ከአገሪቱ ሁኔታ ነው። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ታሳቢ የተደረገ ነውም ተብሏል። ከእነዚህ መመሪያዎች ሌላ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በጥብቅ የሚቆጣጠሩበት መመሪያም ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ