ትናንት ይፈታል ተብሎ የነበረው ቴዲ አፍሮ ሳይፈታ ቀረ
መጻሕቶቹን ለላይብረሪ፣ ልብሶቹን ለእስረኞች አከፋፈለ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. August 13, 2009)፦ ታዋቂው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2001 ዓ.ም. ጠዋት ከእስር እንደሚለቀቅ በስፋት ተወርቶ የነበረ ቢሆንም፤ አድናቂዎቹና ቤተሰቦቹ ቃሊቲ እስር ቤት ሄደው ለረዥም ሰዓታት ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ባዷቸውን ተመልሰዋል።
ቴዲ አፍሮ በእስር ቆይታው ከቤተሰቦቹና ከአድናቂዎቹ ይገቡለት የነበሩትን በርካታ መጻሕፍት ለእስር ቤቱ ቤተመጽሐፍ በስጦታ ያበረከተ ሲሆን፤ ልብሶቹንና እስር ቤት ሲገለገልባቸው የነበሩትን ቁሳቁሶች ለእስረኞች በስጦታ አበርክቶ፤ በትናንትናው ዕለት እንደሚፈታ በነበረው መረጃ መሰረት ሲጠባቅ እንደነበር የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጠቁመዋል።
ረቡዕ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ እናቱ ጥላዬ አራጌ (ራዬ) ቀደም ሲል ዘወትር ረቡዕ ገብታ እንድታየው በተፈቀደላት መሠረት ቃሊቲ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ገብታ የወጣች ሲሆን፤ ውጭ ቆመው የሚጠባበቁ እስረኞች ምን ተባለ በማለት በጥያቄ ሲያጣድፉአት “ምንም የተለወጠ ነገር የለም” በማለት ወደመኪናዋ ገብታ ሄዳለች።
ከሰዓት በኋላም በርካታ አድናቂዎቹ ይፈታል በማለት ቃሊቲ በር ላይ ሲጠባቁ ቢውሉም ምንም የተለወጠ ነገር አልነበረም።
ምንጮች እንደጠቆሙት ቴዲ አፍሮ በደረሰው መረጃ መሰረት በትናንትናው ዕለት እንደሚለቀቅ ተነግሮት የነበረ በመሆኑ ከቤተሰቦቹና ከአድናቂዎቹ ይገቡለት የነበሩትን በርካታ መጻሕፍት ለእስር ቤቱ ቤተመጽሐፍት እንዲሁም ልብሶቹንና እስር ቤት ሲገለገልባቸው የነበሩትን ቁሳቁሶች ለእስረኞች በስጦታ አበርክቶ ባዶውን ሲጠባበቅ ነበር።
ቴዲ አፍሮ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ስድስት ዓመት እስራትና 18 ሺህ ብር ከተወሰነበት በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ ቅጣቱ ወደ ሁለት ዓመት እስርና 13 ሺህ ብር ዝቅ ብሎለት የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ላይ ዓቃቤ ሕግ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ይግባኝ አቅርቦ ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ የቆየ ቢሆንም ሰበር ሰሚ ችሎቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቶለት እንደነበር ይታወሳል። ምንጮች እንደጠቆሙት በዚሁ መሰረት አመክሮው ተቆጥሮለት በትናንትናው ዕለት ከእስር እንዲለቀቅ መፈቻ ተጽፎለታል ነበር።



