ቀነኒሳ በቀለ አምስተኛውን የጎልደን ሊግ ወርቅ አገኘ
የአንድ ሚሊዮን ዶላሩን ጃክ ፖት ለመቋደስ አንድ ውድድር ይቀረዋል
Ethiopia Zare (ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. August 28, 2009)፦ በዛሬው ዕለት ማምሻውን በስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በተደረገው የ2009ኙ የጎልደን ሊግ 5ኛ ዙር ውድድር ላይ ቀነኒሳ በቀለ በ5000 ሜትር አንደኛ በመሆን ውድድሩን አሸነፈ። የአንድ ሚሊዮን ዶላሩን ጃክ ፖት ለመቋደስ ከቀሩት ሦስት አትሌቶች ውስጥ አንዱ ሆኗል።
ዛሬ ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. (ኦገስት 28 ቀን 2009 እ.ኤ.አ.) በተደረገው የ5000 ሜትር የወንዶች የሩጫ ውድድር ላይ ከተሳተፉት አሥራ አምስት አትሌቶች ውስጥ አስራ አንዱ በትውልድ ኬንያዊ ሲሆኑ፣ አሥሩ ለኬንያ ሮጠዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን፣ አንድ ኳታር (በትውልድ ኬንያዊ)፣ አንድ ኡጋንዳ እና አንድ አሜሪካዊ ናቸው።
አትሌት ቀነኒሳ ውድድሩን የጨረሰው በ12፡52፡32 ደቂቃ ሲሆን፣ ኬንያዊው ኤድዊን በ12፡55፡03 ደቂቃ ሁለተኛ፣ አሜሪካዊው ዳታን ሪትዝነሄይን በ12፡56፡27 ደቂቃ ሦስተኛ ወጥተዋል። ከአትሌት ቀነኒሳ ጋር በውድድሩ የተሳተፈው በቀና ዳባ ውድድሩን ሳይጨርስ አቋርጣል።
ኮከቡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊኑ የ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5,000 እና በ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት በዓለም የመጀመሪያው አትሌት ከሆነ ከአምስት ቀናት በኋላ ብዙም ዕረፍት ሳያደርግ ነው በዙሪኩ (ስዊዘርላንድ) የጎልደን ሊጉ 5ኛ ዙር ውድድር ላይ የተሳተፈው።
ከዛሬው በፊት በተደረጉት በአራቱ የጎልደን ሊጉን ውድድሮች ካሸነፈ በኋላ፤ በ10,000 ሜትር ርቀት በተከታታይ አራት ጊዜ በማሸነፍ በርቀቱ የዓለም ሻምፒዮናነቱን በበርሊኑ 12ኛው ሻምፒዮና ማረጋገጡን ተከትሎ በ5000 ሜትሩም ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ዓለምን እጅግ አስደንቋል። ዓለም መቼም ሊረሳው የማይችለው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴም እንዲህ ያለውን ድንቅ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉ፤ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን በርቀት ሩጫው እስካሁን ድረስ ከነበሩትና ካሉት የዓለም አትሌቶች ልዩ ያደርገዋል።
በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን ጁላይ 14 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. (ሰኔ 7 ቀን 2001 ዓ.ም) በተጀመረው የኤ.ኤፍ. ጎልደና ሊግ ውድድር በ5000 ሜትር፣ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ጁላይ 3 ቀን 2009 (ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም.) በ5000 ሜትር፣ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ላይ ጁላይ 10 ቀን 2009 (ሐምሌ 3 ቀን 2001) በ5000 ሜትር እና በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላይ ጁላይ 17 ቀን 2009 (ሐምሌ 10 ቀን 2001 ዓ.ም.) በ3000 ሜትር በተደረጉት ውድድሮች አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማግኘቱን መዘገባችን አይዘነጋም። የመጨረሻውና ስድስተኛው ዙር የጎልደን ሊግ ውድድር በቤልጅየም ዋና ከተማ ብረስልስ ላይ ዓርብ ሴፕቴምበር 4 (ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም.) ይካሄዳል።
በያዝነው 2009 ከዓለም አትሌቶች በቀዳሚነት የአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ተቋዳሽ ናቸው ተብለው የሚጠበቁት ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ራሻዊቷ ይሌና ኢሲንባዬቫ ናቸው። በ2006 እ.ኤ.አ. በተካሄደው የጎልደን ሊግ የአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ተቋዳሽ ከነበሩት የዓለም አትሌቶች ውስጥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እንደነበር አይዘነጋም። የዛሬው አምስተኛው ዙር ውድድር ከመጀመሩ በፊት ከወንዶች አትሌት ቀነኒሳና ሦስት ሴቶች የአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ጃክ ፖት ተቋዳሽ ይሆናሉ ተብለው ተጠብቀው ነበር። እነርሱም ራሺያዊቷ ይሌና ኢሲንባዬቫ በምርኩዝ ዝላይ፣ ጃማይካዊት ኬሮን ስትዋርት በ100 ሜትር እና አሜሪካዊቷ ሳኒያ ሪቻርድ በ400 ሜትር ነበሩ።
ጃማይካዊቷ ኬሮን ስቱዋርትን አሜሪካዊቷ ካርምሊታ ጄተር ቀድማት በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን ስትወስድ፣ ኬሮን የብር ሜዳሊያ ለመውሰድ ተገድዳለች። በዚህም ምክንያት የአንድ ሚሊዮን ዶላሩን ይቋደሳሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩትን አትሌቶች ቁጥር ከአራት ወደ ሦስት ዝቅ ብሏል። አትሌት ኬሮን ከጃክ ፖቱ ተቋዳሾች ዝርዝር ውስጥ ወጥታለች። ራሺያዊቷ ይሌና ኢሲንባዬቫ የዓለም ክብረወሰን (ሪከርድን) በዛሬው ዕለት በማሻሻል ነው ውድድሯን ያጠናቀቀችው። ያስመዘገበቸው ርቀት 5 ሜትር ከስድስት ሴንቲ ሜትር ነው።
የአንድ ሚሊዮን ዶላሩን ጃክ ፖት ለመካፈል የፊታችን ሴፕቴምበር 4 በሚደረገው ውድድር ተፋጥጠው የሚጠባበቁት ይሌና ኢሲንባዬቫ፣ ሳኒያ ሪቻርድስ እና ቀነኒሳ በቀለ መሆናቸውን በዛሬው ዕለት የተደረጉት ውድድሮች ውጤት ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለኮከቡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ መልካም ዕድል ትመኝለታለች።
በዚሁ የዙሪኩ ጎልደን ሊግ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነችውና የባህሬይኗ አትሌት ማሪያም ጀማል በ1500 ሜትር የሴቶች የሩጫ ውድድር አንደኛ ወጥታለች። ማሪያም ውድድሩን የጨረሰችው በ3፡59፡15 ደቂቃ ነው። ማሪያም በርቀቱ የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና መሆንዋ ይታወቃል።



