ቀነኒሳ የራሱን የኦሎምፒክ ክብረወሰን ሰበረ

አጓጊና ልብ አንጠልጣይ ውድድር ነበር

Kenenisa Bekele celebrates, Beijing Olympic 2008, Aug 17
 

Ethiopia Zare (እሁድ ነኀሴ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. August 17, 2008)፦ ዛሬ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በራሱ የተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል አንደኛ ሲወጣ፣ አትሌት ስለሺ ስህን ሁለተኛ፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ደግሞ ስድስተኛ በመውጣት ውድድሩን ጨርሰዋል። 

 

አትሌት ቀነኒሳ ውድድሩን የጨረሰው በ27፡01.17 ደቂቃ ሲሆን፣ ስለሺ ስህን ደግሞ በ27፡02.77 ደቂቃ ሁለተኛ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ደግሞ በ27፡06.68 ደቂቃ ስድስተኛ ወጥተዋል።

 

ውድድሩ እጅግ አጓጊና ልብ አንጠልጣይ ነበር። ሦስት ኬንያውያን፣ ሦስት ኤርትራውያን እና ሦስት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉበት ሲሆን፣ በመጨረሻዎቹ ዙሮች ላይ ሦስት ኬንያውያን እና ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ ከቀነኒሳ፣ ስለሺ እና ኃይሌ ጋር እግር ለእግር ተከታትለው ሮጠዋል። 

 

Seleshi, Kenenisa, Haile (right to left)አትሌት ቀነኒሳና ስለሺ የመጨረሻው ዙር ላይ ተፈትልከው የወጡ ሲሆን፣ ቀነኒሳ በአስገራሚ ሁኔታ ፍጥነት በመጨመር የዛሬ አራት ዓመት ኦገስት 20 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. አቴንስ ግሪክ ላይ ሰብሮት የነበረውን 27፡05.10 ደቂቃ የኦሎምፒክ ክብረወሰን በዛሬው ዕለት በ3.53 ደቂቃ በማሻሻል ውድድሩን በአንደኝነት ጨርሷል። በ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን የተያዘው በራሱ በቀነኒሳ በቀለ ብራስልስ ቤልጅየም ውስጥ 26፡17.53 ደቂቃ ኦገስት 26 ቀን 2005 እ.ኤ.አ. የተመዘገበው ነው።

 

ኬንያዊያኖቹ ሚቻ ኮጎ በ27፡04.11 ደቂቃ ሦስተኛ እና ሞሰስ ንዲያማ ማሳይ በ27፡04.11 ደቂቃ አራተኛ፣ ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ በ27፡05.11 ደቂቃ አምስተኛ፣ ኬንያዊው ማርቲን ኢሩንጉ ደግሞ በ27፡08.25 ደቂቃ ሰባተኛ ወጥቷል።

 

የ10 ሺህ ሜትሩ ውድድር እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ በአንድ ወርቅ ብቻ 36ኛ ደረጃ ላይ ከታይላንድ፣ ሕንድ እና ቱኒዚያ ጋር ትገኝ የነበረ ሲሆን፣ የቀነኒሳ ወርቅ እና የስለሺ ብር ሲጨመርበት፤ በድምሩ በሁለት ወርቅ እና በአንድ የብር ሜዳሊያ ደረጃዋ ከፍ ብሎ 22ኛ ላይ ለመገኘት አስችሏታል።

 

የሴቶች ማራቶን

 

በቤጂን ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል (7፡30 AM / 07:30) ላይ በተደረገው የሴቶች ማራቶን ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳትፈዋል። አትሌት ድሬ ቱኔ ውድድሩን በ2፡31፡16 ሰዓት በመጨረስ 15ኛ ስትወጣ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ሳይጨርሱ ቀርተዋል።

 

ኤርትራዊቷ አትሌት ነቢያት ሀብተማርያም ደግሞ በ2፡37፡03 ሰዓት በመግባት ውድድሩን በ47ኝነት አጠናቃለች።

 

በሴቶች ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ሩማኒያዊቷ ኮንስታንቲና ቱምኩ ስትሆን በ2፡26፡44 ሰዓት ውድድሩን አጠናቃለች። በ2፡27፡06 ሰዓት በመግባት ሁለተኛ የወጣችው ኬንያዊቷ አትሌት ክርስቲና ንደሬባ ስትሆን፣ ሦስተኛ የወጣችው ቻይናዊቷ አትሌት ቹንሱ ሱሁ በ2፡27፡07 ውድድሩን ጨርሳለች።

 

የሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል ፍፃሜ

 

በቤጂንግ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ማምሻውን ሦስት ሰዓት ተኩል (9:30 PM / 21:30) ላይ በተደረገው የሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያውን ከሦስቱ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በብቸኝነት ያለፈችው አትሌት ዘምዘም አሕመድ ውድድሩን በ9፡17.85 ደቂቃ በመጨረስ 7ኛ ወጥታለች።

 

ይህንን ርቀት በአንደኝነት የጨረሰችው የሰላሳ ዓመቷ ራሺያዊት ጉልናራ ጋልኪና-ሳሚቶቫ ከዘጠኝ ደቂቃ በታች በመግባት የዓለምና የኦሎምፒክን ክብረወሰን ሰብራለች። ሄርካሊዮን ግሪክ ላይ ጁላይ 4 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. 9፡01.59 ደቂቃ በመግባት የዓለምን ክብረወሰን የያዘችው ራስዋ ጉልናራ የነበረች ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ውድድሩን በ8፡58.81 ደቂቃ በመጨረስ ክብረወሰኑን ለማሻሻል ችላለች። (ቀሪዎቹን ውድድሮች ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድና ቀሪዎቹን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድር ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድ ያዘጋጀነውን የውድድሩን የጊዜ ሠሌዳ እዚህ በመጫን ያገኙታል!)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ