Kenenisa Bekele, Beijing olympic, 20080823, 5000 men

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ነኀሴ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. August 23, 2008)፦ በዛሬው ዕለት በቤጂንግ ኦሎምፒክ በተካሄደው የወንዶች 5 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ሩጫ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለ24 ዓመታት በሞሮኮዋዊው ሰዒድ አዊታ ተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክ ክብረወሰን በመስበር ለኢትዮጵያ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በ10 ሺውም የኦሎምፒክ ክብረወሰንን መስበሩ አይዘነጋም።

 

ቀነኒሳ ውድድሩን የጨረሰው በ12፡57.82 ደቂቃ ሲሆን፣ የኦሎምፒኩን ክብረወሰን በስምንት ሰኮንዶች አሻሽሎታል።

 

በ5 ሺህ ሜትር በዛሬው ዕለት ከቀነኒሳ ጋር አብረውት የተወዳደሩት አትሌት አብርሃም ጨርቆስ በ13፡16.46 ደቂቃ አምስተኛ ሲወጣ፣ አትሌት ታሪኩ በቀለ (የቀነኒሳ ወንድም) ደግሞ በ13፡19.06 ደቂቃ ስድስተኛ ወጥቷል።

 

ኬንያውያኖቹ ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በ13፡02.80 ደቂቃ ሁለተኛ፣ ኤድዊን ቼሩዮት ሶይ በ13፡06.22 ደቂቃ ሦስተኛ ወጥተዋል። አራተኛ የወጣው ኡጋንዳዊው ሞሰስ ንዲኤማ ኪፕሲሮ በ13፡10.56 ደቂቃ ውድድሩን በመጨረስ ነው።

 

አትሌት ቀነኒሳ ለራሱ ሁለተኛውን፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማስገኘቱ፤ ኢትዮጵያ በአራት ወርቅ፣ በአንድ የብር እና በአንድ የነኀስ ሜዳሊያዎች በሜዳሊያ ሠንጠረዥ የ18ኛ ደረጃነትን ይዛለች። ቀነኒሳ በቀለ ባለፈው እሁድ ነኀሴ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. August 17, 2008 በ10 ሺህ ሜትር በራሱ ተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክን ክብረወሰን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ አይዘነጋም።

 

አትሌት ቀነኒሳ በአሁኑ ወቅት በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትሮች የዓለም እና የኦሎምፒክም ክብረወሰኖች ባለቤት ለመሆን በቅቷል።

 

የቤጂንጉ የ2008 እ.ኤ.አ. ኦሎምፒክ ነገ የሚፈፀም ሲሆን፣ የወንዶች ማራቶን በነገው ዕለት ይካሄዳል። በዚህ የወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ