የዓመቱ ታላቅ ሰው የሽልማት ሥነሥርዓት ተካሄደ
የብርቱካን የልጅነት ጓደኛ ሽልማቱን ተቀበለች
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2001 ዓ.ም. September 8, 2009)፦ በእስር ላይ የምትገኘው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የ2001 ዓ.ም. ድንቅ ሰው በመባል ተሸለመች። የሽልምት ሥነሥርዓቱም እሁድ ሴፕቴምበር 6 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. በቫንኩቨር ካናዳ ተካሄደ።
በኢትዮጵያ ፍትሃዊ ሥርዓት ለማስፈን በመታገል የምትታወቀው ወ/ት ብርቱካን ለዚህ ሽልማት የበቃችው ለሰብዓዊ መብት መከበርና የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ መርጋት በግል ሕይወቷ ላይ ተግባራዊ በማድረጓ፣ በአምባገነኑ የኢህአዲግ አገዛዝ በጉልበት የተጨናገፈውና በዲሞክራሲያዊው ምርጫ 97 ምክንያት በታሰሩት የቅንጅት አመራር አወዛጋቢ የአፈታት ሂደት ላይ ወ/ት ብርቱካን የተፈጸመውን የአፈታት እውነታ ቁልጭ አድርጋ በማስረዳቷ ምክንያት ኢፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለዕድሜ ልክ እስራት በመዳረጓ መሆኑ ከአዘጋጆቹ ተገልጿል።
ወ/ት ብርቱካን የሠላማዊ ትግል ሂደትን ለማጠናከር በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሳ አንድነት ፓርቲን ከመሰረቱ ግለሰቦች አንዷ ከመሆኗም በላይ፤ በቅንነት ንጹኅ የፖለቲካ ሂደት በተቃዋሚዎች ጎራ እንዲሰፍን ያደረገችው አስተዋጽዖም ከግምት ውስጥ መግባቱን ለማወቅ ችለናል።
በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙትና ሽልማቱን እንዲሰጡ የተጋበዙት አቶ ሼክስፒር ፈይሣ በሲያትል የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በብርቱካን ላይ ያላቸውን እምነትና በተለይም የቅንጅት አመራሮች ከእስር ተፈተው በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ለኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል በላከችው መልዕክት “ይሄ ስለእኔ አይደለም። ይሄ ስለኢትዮጵያ ነው። የኔ ክብር የኔ ኩራት፣ የኔ የበታችነት ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው። ለኢትዮጵያ የሚበጅ ከሆነ የኔ መዋረድና መለመን ለኢትዮጵያ ማድረግ የምችለው ትንሽ ነገር ነው” በማለት የተናገረችውን በማውሳት፤ ወ/ት ብርቱካን ለፖለቲካ አጋሮቿ ያላትን ፍቅርና አክብሮት፤ ከምንም በፊት ለሀገሯና ለህዝቧ ያላትን ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወ/ት ብርቱካንን ወክላ ሽልማቱን የተቀበለችው ወ/ሮ ሰናይት የ7ኛና የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ከወ/ት ብርቱካን ጋር አንድ መቀመጫ ላይ ተቀምጠው የተማሩ መሆናቸውን ገልጻ፤ ብርቱካን ከልጅነቷ ጀምራ አንደኛ የምትወጣ ጎበዝ ተማሪ ከመሆኗም በላይ የምትጽፋቸውን ግጥሞችና መጣጥፎች ለተማሪዎች ታነብ እንደነበር አስታውሳለች። ከረዥም ጊዜ በኋላ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ቤት ስትመለስ ታናናሽ ወንድሞቿን ስለብርቱካን ስትጠይቅ ዳኛ መሆኗን እንደሰማችና ይህንን ሽልማት በስሟ ስትቀበልም ታላቅ ክብር እየተሰማት መሆኑን የእንባ ሳግ እየተናነቃት ንግግሯን በመቋጨት ሽልማቱን ተቀብላለች።
ሽልማቱ አንድ ሺህ የካናዳ ዶላርና ወርቅ ቅብ ፕላክ ሲሆን፣ በቀጥታ ለቤተሰቦቿ የሚላክ እንደሚሆን ተገልጿል። አዘጋጆቹ በካናዳ የሚገኙ የሲቪል ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች መሆናቸው ታውቋል።



