የአንድነት መሪ ወ/ት ብርቱካን የዓመቱ ድንቅ ሰው ተብላ ተሸላሚ ሆነች
Ethiopia Zare (ረቡዕ ነሐሴ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. September 2, 2009)፦ የሕግ የበላይነትን፣ ዲሞክራሲንና ነፃነትን በግል ሕይወቷ ላይ ተግባራዊ ያደረገችው የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የ2001 ዓ.ም. የዓመቱ ድንቅ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነች።
ተሸላሚዋ ለዚህ ታላቅ ሽልማት የተመረጠችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከነበረችበት ጊዜ፣ ተመርቃ በሥራ ገበታ ላይ በነበረችባቸው ጊዜያት በቅንነትና ፍትህን በማስከበር ረገድ ህዝብን በታማኝነት ስታገለግልን ከመቆየቷም በላይ ተንበርካኪ ሳትሆን ሕግ የሀገሪቱ የበላይ ገዢ እንዲሆን ባደረገችው አገልግሎትና በፖለቲካው ዓለምም ዘልቃ በመግባት ከፍተኛ ለውጥ አራማጅ የሆነውን ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲን በተቀዳሚ ም/ሊቀመንበርነት በመምራት ካበረከተችው አስተዋጽዖም በተጨማሪ አንድነት የተሰኘውን ፓርቲ ከአጋሮቿ ጋር በመመስረት በምታምንበት የሠላማዊ ትግል እንቅስቃሴ መጎልበት ባደረገችው አስተዋጽዖ ነው።
ወ/ት ብርቱካን አሁን በኢህአዲግ አገዛዝ ተይዛ ወደ እስር የተጣለችው ሕግ የሀገሪቱ ጠቅላላ ገዥ መሆን አለበት በሚል ጽኑ እምነቷ ከዚህ በፊት ከእስር የተፈታችበትን የይስሙላ ይቅርታ ጥያቄ በግልጽ ማስቀመጧ ለፍትህ አስፈላጊነት ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ በመሆኑ ለዚህ ሽልማት ያበቃት መሆኑን አዘጋጆቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።
ሴፕቴምበር 6 ቀን 2009 በቫንኩቨር ካናዳ የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ የሽልማቱ አዘጋጆች በአጠቃላይ ካናዳ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጰዊያኖች መሆናቸው ታውቋል። በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ነዋሪነቱ ሲያትል የሆነው የሕግ ጠበቃ ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሣ በክብር እንግድነት እንደሚገኝና የ2009 የሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ስፖርት ውድድር ላይ የሚሳተፉ የቫንኩቨር፣ የሲያትል፣ የፖርትላንድ፣ የዌኒፔግ የካልጋሪ፣ የኤድመንተንና የቪክቶሪያ አካባቢ ነዋሪዎች በአስተናጋጇ ቫንኩቨር ይገኛሉ።
ቫንኩቨር በሴፕቴምበር 5 እና 6 የሚካሄደው የስፖርት ውድድር አስተናጋጅ ስትሆን፣ የሕፃናት ስፖርት ውድድርን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛዎች ተዘጋጅተዋል። በሁለቱም ቀናት አንጋፋዋ አርቲስት ማርታ አሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቿን የምታቀርብ ሲሆን፣ ዝነኛው ወጣት ድምፃዊ አብዱ ኪያርም በሴፕቴምበር 5 በቫንኮቨር የሙዚቃ ኮንሰርት የሚያዘጋጅ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ከመዝናኛው ባሻገር ታላቋ የፖለቲካ ሰው ወ/ት ብርቱካን ተሸላሚ የሆነችበት የዓመቱ ታላቅ ሰው ሽልማት መደረጉ ባብዛኛው የአካባቢውን ሰው እጅግ ያስደሰተ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ አዘጋጅ ከስፍራው አረጋግጧል።



