ቴዲ አፍሮ ከኢትዮጵያ ዛሬ ጋር ቃለምልልስ አደረገ
የፊታችን ቅዳሜ ዲሴምበር 5 በስቶክሆልም የሙዚቃ ድግስ ያቀርባል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ኅዳር 23 ቀን 2002 ዓ.ም. December 2, 2009)፦ የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ከእስር የተፈታውና በውጭ ሀገራት የሙዚቃ ኮንሰርቱን እያካሄደ ያለው አርቲስት ቴዲ አፍሮ ሰኞ ማምሻውን ስቶክሆልም የገባ ሲሆን፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ዛሬ ጋር ቃለምልልስ አደረገ።
በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በሚገኘው የኦርላንዳ አየር ማረፊያ ሲደርስ የሀገር ባህል ልብስ የለበሱ ሁለት ወጣት ሴቶች አበባ ያበረከቱለት ሲሆን፣ ቅዳሜ ዲሴምበር 5 በስቶክሆልም የሚካሄደው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት አዘጋጅ አቶ ሙሉሰው ዋቄም በስፍራው ተገኝቶ ነበር።
አርቲስት ቴዲ አፍሮ ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ባደረገው ቃለምልልስ ለቀረቡለት የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል። በቃለምልልሱ ላይ የቀረቡለት ጥያቄዎች፤ ከኮንሰርቱ ጋር በተያየዙ ተነስተው በነበሩ ጉዳዮችና ወሬዎች፣ በእስር ቤት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመርዳት ያደረገውን ጥረትና ወደፊትም ስለሚያደርገው እርዳታ፣ “ያስተሰርያልን” በስታዲየም ለምን እንዳልዘፈነ፣ … እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን የዳሰሱ ናቸው።
በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ባለፈው ሣምንት ኖቨምበር 28 የተካሄደውን የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት አንዳንድ ወገኖች ቦይኮት ለማስደረግ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑ አፍቃሪዎቹ ታዳሚ እንደነበሩና በዝግጅቱም እንደረካ ገልጿል።
ያሬድ ክንፈ ከቴዲ አፍሮ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ አቀርቦታል። (ሙሉውን ቃለምልልስ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)



