Ethiopia Zare (ሐሙስ መጋቢት 2 ቀን 2002 ዓ.ም. March 11, 2010)፦ ለምርጫው የሁለት ወር ከ15 ቀናት ዕድሜ ቀርቷል። በአዲስ አበባና በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች የኢህአዲግ መንግሥት ልዩ ወታደራዊ የጥበቃ ኃይሎችን እያሰማራ መሆኑ ተገለጸ።

 

የፌደራሉና የአዲስ አበባ ፖሊስ አንዳንድ የቀድሞ አዛዦች፤ ከመከላከያ ሠራዊቱ በተዛወሩ የጦር ኃይሉ አዛዦች እየተተኩ ነው። ጉዳዩ የተፈጠረው “በፖሊስ አዛዦቹ ላይ እምነት በመታጠቱ ነው” የሚል ምክንያት ተሰጥቷል።

 

የደህንነት ሰዎች፣ ካድሬዎች፣ በቀበሌ ገበሬ ማኅበራት የሚገኙ የገዥው ፓርቲ ታማኝ አገልጋዮች፣ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት፣ … የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና የደጋፊዎቻቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉ እየተከታተሉ ሲሆን፤ በበርካታ ሥፍራዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩ ተመራጮች፣ አባላትና አደራጆች ብሎም ጠንካራ ደጋፊዎች ጠንከር ያለ ወከባ እየተፈጸመባቸው ነው። ይህ ሁኔታ በትግራይንና የምሥራቅ ጎጃም ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አካባቢ በአደባባይ ግድያን ጨምሮ እስር፣ ወከባና ተመራጮችን ከመደለል አልፎ እስከማስፈራራት የዘለቁ ሂደቶች ሲታዩ ሰንብተዋል።

 

ይህ በእንዲህ እያለ ተቃዋሚዎች በአገዛዙ በኩል የሚመጡትን ማናቸውንም ተጽዕኖዎች ተጋፍጠው የአገዛዙን ምንነትና በሀገሪቱ ያለውን ስቃይ ለህዝቡና ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ከማሳወቅ ወደኋላ አንልም በማለት እልህ አስጨራሽ ትግላቸውን እንደሚገፉበት ይፋ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

 

በአዲስ አበባ መሰል ጫናዎች በግልጽ ባይታዩም የ1997 ዓ.ም. ዐድማ በታኝ የፖሊስ ኃይሎች እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ክምችት ከወዲሁ በግልጽ እየታየ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሣሪያ ያነገቡ የጦር ሠራዊቶችና የፌደራል መኪኖች መበራከታቸውንም የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል።

 

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ይሄን መሰሉን ሁኔታ “ዕባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል …” ብለውታል። ትርጓሜው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ “በቢላዋ ቀልድ የለም አለች ዶሮ” ሲሉ የተረቱበትን የምርጫ 97ትን ስጋት በግልጽ ያመለክታል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ