“አንድነት ሊዘጋ ይችላል” ኢንጂ. ግዛቸው

Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. January 8, 2010)፦ በኢህአዲግ ካድሬዎች አስገዳጅነት በአማራ ክልል የሚገኙ የአንድነት አባላት ወደ መኢአድ እንዲቀየሩ እየተገደዱ መሆኑን ወደ አዲስ አበባ የገቡ የአንድነት አባላት ገለጹ።

 

ሰሞኑን ከምሥራቅ ጎጃም እንደመጡ የገለጹና በአዲስ አበባው አንድነት ጽ/ቤት የተገኙት አባል እንደገለጹት ለመኢአድ በሰፊው የሚከፈቱ በሮች ለአንድነት የተዘጉ ሲሆን፤ በአንድነት አባላት ላይ ክትትልና ማስፈራሪያ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

 

እኚህ አባል ጨምረው እንደገለጹት እንግልቱን በመጥላት ጥቂት አባላቶች ወደ መኢአድ የተቀየሩ ሲሆን፣ ባመጹት ላይ እስር እየተፈጸመ ነው ብለዋል። ሁኔታውን በሚመለከት መኢአድ ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፤ በቅርቡ መግለጫ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው በኬንያ ለሚታተመው ዕለታዊው ጋዜጣ “ዴይሊኔሽን” የአንድነት አባላት እስር ስጋት ላይ እንደጣላቸውና ድርጅቱም ሊዘጋ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፤ ገዢው ፓርቲ አንድነትን በመከፋፈል ለመበታተን ያልተቋረጠ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ኢህአዲግ ባሰራጨው “የጨለማው ጉዞ” ዶክመንተሪ ፊልም የቀድሞ የድርጅቱ አባልና ሞት የተፈረደበት አቶ መላኩ ተፈሪ ድርጅቱን በማጥላላት የተናገረ ሲሆን፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጥቂት አምባገነኖች የሚመሩ ውስጣቸው ባዶ ነው ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና በመንግሥት መገናኛ ብዙኅን በተላለፈ ፕሮግራም ላይ ተደምጧል።

 

“መርኅ ይከበር!” በሚል ከድርጅቱ የተባረሩ አባላት ደግሞ በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ብርሃን፣ በወላይታ፣ በቦንጋ እና በሌሎችም ክልሎች ደጋፊዎቻቸውን እያበራከቱ ከመሆኑም በላይ በድርጅቱ ስላለው ንቅዘት በይፋ በማጋለጥ ተሰሚነት እያተረፉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

 

አስተባባሪው አቶ አንተነህ ማስረሻ በፓርቲው ውስጥ የተሰገሰጉ ሕገ-ወጥ አባላትን በየክልሉ ለሚገኙ የድርጅቱ አባላት የማጋለጥ ሥራና የድርጅቱን ንቅዘት እናሳውቃለን ብለዋል። ከምሥራቅ ሸዋና ከባሌ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን አካሄድ የተቃወሙ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው የሚገልጹት አቶ አንተነህ፤ እንቅስቃሴውን የሚያደርጉት ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ መሆኑን ጠቁሟል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!