Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 24 ቀን 2002 ዓ.ም. January 2, 2010)፦ በኢትዮጵያ በመጭው ግንቦት 15 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ የብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ታህሣስ 22 ቀን በጽ/ቤቱ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ የሚካሄድባቸውን ሥፍራዎች ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

 

ይሄን ተከትሎ የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ትናንት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በሁሉም አካባቢዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ባሳተፈ ሁኔታ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ፤ ከምርጫው የምንወጣበት ሁኔታ ይኖራል” ሲሉ አገዛዙን ማስጠንቀቃቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

ዶ/ር መራራ ከዚህ ቀደም ተቃዋሚዎች ሳያውቁት በኅዳር ወር መጨረሻ 2002 ዓ.ም. የተካሄደውን የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በጥብቅ ኮንነው፤ ምርጫ ቦርዱ ግን ቀደም ሲል በተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫው ሊደገም የማይችልበት ሁኔታ እንደሌለ ግልጽ አድርጓል።

 

547 ወንበሮች ይኖሩታል በሚባለው ፓርላማ ገዥው የኢህአዲግ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የሀገሪቱ የምርጫ ጣቢያዎች ዕጩዎችን የሚያቀርብ ሲሆን፤ በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ እና የአቶ ልደቱ አያሌው ኢዴፓ በመጭው ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

ምርጫ በሚካሄድባቸው ክልሎች መሰረት በአዲስ አበባ 23፣ በድሬደዋ 2፣ በትግራይ 38፣ በአፋር 8፣ በአማራ 138፣ በኦሮሚያ 178፣ በደቡብ ህዝቦች 123፣ በቤንሻንጉል 9፣ በጋምቤላ 3፣ በሐረሪ 2፣ በሶማሌ 23 መቀመጫዎች ለምርጫ መመደባቸውንም ለማወቅ ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!