ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ Artist Tilahun Gesseseሙሉ ታሪኩን የያዘ መጽሐፍ ይመረቃል፣ በስሙ አደባባይ ይሰየማል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 7 ቀን 2002 ዓ.ም. April 15, 2010)፦ የዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ አንደኛ የሙት ዓመት ከሚያዝያ 15 ቀን እስከ 17 ድረስ በሚቆይ ልዩ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከበር ተገለጸ። 

 

ይህ የተገለጸው ባለቤቱ ወ/ሮ ሮማን በዙ እና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ከባህል ምክትል ሚኒስትር ማሕሙድ ጋዓስ ጋር በመሆን ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 7 ቀን 2002 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ከዛንቺስ በሚገኘው ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

 

”በበዓሉ ላይ የሱዳን የባሕል ቡድን አባላት ሊገኙ እንደሚችሉ በአዲስ አበባ የካርቱም አምሣደር አማካኝነት ይሁንታ አግኝቻለሁ፣ የጃፓን የሙዚቃ ሰዎችም “ጃፓኗን ወድጄ” የሚለውን የጥላሁንን ዜማ ለማጀብ እንደሚገኙ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል ወ/ሮ ሮማን።

 

የጥላሁንን መታሰቢያ ሐውልት “ማንነት ጥበብ ስቱዲዮ” ጨረታውን አሸንፎ የቀረጻውን ሥራ መጨረሱን ያስታወቁት ወ/ሮ ሮማን፤ “የጥላሁን ገሠሠን ሥራዎች በሲዲ አሳትሞ ለማሠራጨት የኮፒራይቱ ጥያቄ እና እነማን በእሱ ሥራ ተሳትፎ አድርገዋል የሚለው በቅድሚያ እየታየ ነው” ሲሉ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

 

አስቀድሞ ይፋ በሆነው የጥላሁን ገሠሠ አንደኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ ዝግጅት ዝርዝር መግለጫ መሠረት፤ በአዲስ አበባ ስታድየም መግቢያው በነፃ የሆነና የጥላሁን ሥራዎች ብቻ የሚቀርቡበት፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በሙሉ የሚታደሙበት የሙዚቃ ዝግጅት ዓርብ ሚያዝያ 15 ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ይካሄዳል።

 

በማግስቱ ሚያዝያ 16 ቀን የሐውልት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት እና የቁርስ መስተንግዶ በሥላሴ ቤተክርስቲያን እና በመኖሪያ ቤቱ እንደዚሁም ከቀትር በኋላ የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ ከልደት እስከ ሞት የሚተርከው መጽሐፍ ምረቃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መኰንን አዳራሽ ከ11 ሰዓት እስከ 12፡30 ሰዓት ይካሄዳል።

 

ከዚህ በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም፤ እውቁን የሙዚቃ ሰው የሚመለከት የአልባሳትና የፎቶ ዐወደ-ራዕይ ይቀርባል። ይህ ዐውደ-ራዕይም ለአንድ ወር ያህል ለተመልካች ክፍት ይሆናል። እሁድ ሚያዝያ 17 ቀን ደግሞ አምስት መተላለፊያ መንገዶች በሚቀናጁበትና በመሿለኪያ የቀድሞ አራተኛ ክ/ጦር በሚገኝበት ሥፍራ የሚገኘው አዲስ አደባባይ በጥላሁን ገሠሠ ስም መሰየሙን የሚገልጽ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ