Teddy Afro
  • በችሎቱ ብዙ ደህንነቶች ነበሩ
  • 20 ሰዎች ታስረዋል

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. April 29, 2008)፦ ታዋቂው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የዋስትና መብት የማይሰጠው መሆኑንና ክሱን በእስር ቤት ሆኖ እንዲከታተል ዛሬ የዋለው ችሎት መወሰኑን የአዲስ አበባው ሪፖርተራችን ከችሎት ዘገበ።


 

ቴዲ አፍሮ የተከሰሰበት በ1996 በወጣው የወ/መ/ህ/ቁ 543 ንዑስ ቁጥር 3 ሲሆን የዋስትና መብቱ የተከለከለው በወ/መ/ህ/ቁ 63 ንዑስ ቁጥር 3 መሰረት መሆኑንና ይህም ሕግ የተከሰሰበት ወንጀል አስራ አምስት ዓመት የሚያስቀጣው ከሆነና የተከሰሰበት ሰው የሞተ ከሆነ ተከሳሹ የዋስትና መብቱ ይከለከላል የሚል መሆኑን በፍርደ ገምድልነቱ የሚታወቀው የኢህአዴግ ፍርድ ቤት የገለጸ ሲሆን፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን የተከሰሰበት ወንጀል እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣው በመሆኑና የተከሰሰበት ግለሰብ የሞተ በመሆኑ የዋስትና መብት ሊሰጠው አይገባም ሲል ዛሬ ሚያዝያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. የዋለው ችሎት በ’ማረሚያ ቤት’ ሆኖ ክሱን ይከታተል ሲል መወሰኑን ለማወቅ ችለናል።

 

ዓቃቤ ሕግ ኮከቡ ድምጻዊው ላይ አለኝ የሚለውን ምስክሮችና ማስረጃ ይዞ ለግንቦት 13 እንዲቀርብ የተወሰነ መሆኑንም ሪፖርተራችን አክሎ ገልጿል።

 

በተጨማሪም ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ግለሰቦች ታስረው የተዋከቡ ሲሆን፣ በችሎቱ ውስጥ የህዝቡን ያህል የደህንነት ሰዎች ተሰግስገው እንደነበርና በሦስት ካሜራ በመቅረጽ የህዝቡን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ሪፖርተራችን ዘግቧል።

 

በፍርድ ቤቱ ጀርባ ታግተው የነበሩት ሰዎችም ተፈትሸው የሞባይል ስልኮቻቸውን ከመነጠቃቸውም በላይ ‘ለምን ለሌላው ሰው አልመጣችሁም?’፣ ‘ቴዲ ምን ስለሆነ ነው?’፣ ‘አርፋችሁ ሥራችሁን ለምን አትሠሩም?’፣ ... በማለትና በተለይም ጋዜጠኞችን ‘ወሬ እየለቀማችሁ’፣ ወሬ አቀባባዮች'፤ ... በማለት ለአምስት ሰዓታት ካቆዩዋቸው በኋላ የተወሰኑትን የለቀቁ ሲሆን፣ የቀሩትን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

ይህ የወያኔ ካድሬዎችና የደህንነት ሰዎች ሴሌብሪቲ ወይንም ዝነኛነት ምን ማለት እንደሆነ ምንም እውቀት የሌላቸው እንደሆነ እና ትልቅ ክብር ላለው የጋዜጠኝነት ሙያ ምንም ክብር የሌላቸው መሆኑን የሚያስረዳ ነው ሲሉ አንድ አዛውንት ተደምጠዋል። ቴዲ ዝነኛና በሀገሪቱ ካሉ እውቅ ግለሰቦች አንዱ በመሆኑ አድናቂዎቹ ሥራ መተውም ሆነ አለመተው መብታቸው ሆኖ ሳለ፣ በመኃይማን የደህንነት ስብስብ እንዲህ አይነት ጸያፍ አነጋገር መስማት የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ሆኔታውን ማየታቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው በስፍራው የነበሩት እኝሁ አዛውንት በምሬት መናገራቸው ታውቋል።

 

በተያያዘም ቴዎድሮስ ካሳሁን የዋስትና መብት ሊሰጠው ይገባል፣ ክሱ ሁለት ዓመት የቆና ሆን ተብሎ ድምጻዊውን ለማጥቃት የተነሳ ነው የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በትላንትናው ዕለት ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በር ላይ ሠላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይ ዝነኛው አርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ በርካታ አርቲስቶች መገኘታቸው ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ