በቴዲ አፍሮ ላይ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮቹን ትናንት ፍ/ቤት አቀረበ
ሦስቱም ምስክሮች ፖሊሶች ናቸው

Ethiopia Zare (ኀሙስ ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. May 22, 2008)፦ ትናንት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የነበረው ቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን) ላይ ከሳሹ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቼ ካላቸው አራቱ ውስጥ ሦስቱ ግለሰቦች አቀርበው ነበር። የቀረቡት ሦስቱም የቀረቡት ምስክሮች ፖሊሶች ናቸው።
የመጀመሪያው ምስክር ኮንስታብል ከበደ ወየሳ ሲሆን፣ ከዓቃቤ ሕግ፣ ከቴዲ ጠበቃ እና ከዳኛው ከተሰነዘሩለት ዋና፣ መስቀለኛ እና ማጣሪያ ጥያቄዎች ምስክርነቱን አስረድቷል። እንደዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር አገላለጽ ከሆነ ጥቀምት 23 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ፣ በተለምዶ “ፊት በር” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የጥበቃ ሥራ እየሠራ ባለበት ወቅት፣ አንድ አረንጓዴ የቤት መኪና፣ ግራና ቀኝ በሁለት ላዳ ታክሲ ታጅቦ በፍጥነት እየበረረች ትመጣለች፣ ምስክሩ በ20 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ይመለከታል። አንድ ሰው ደግሞ፣ ከቀበሌው አካባቢ (ከቀኝ ወደ ግራ) አስፋልቱን ወደ ቤተ መንግሥት ሲያቋርጥ፣ መሃል አስፋልት ላይ ይወድቃል። ያች ስትበር የነበረችው አረንጓዴ መኪና፣ የተኛውን ሰው ገጭታው ትሄዳለች። መኪናውን ሮጦ ይከተልና ታርጋ ቁጥሩን ይመዘግባል።
በአራት ኪሎ ግንብ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የሥራ ባልደረባውን ጠርቶ፣ ወደ ወደቀው ልጅ ሲሄድ፣ የመጠጥ መንፈስ እንዳለውና ሕይወቱ እንደነበረች ተመልክቷል። ከዛም ከ5 ደቂቃ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። ስልክ ደውሎም ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቁን ገልጿል። በማግስቱም ትራፊክ ጽ/ቤት ሄዶ ቃሉን መስጠቱን፣ መኪናዋን እዚያ ሲያያት እንዳወቃት ገልጾ፣ ተከሳሹን ቴዲ አፍሮን ግን አላውቀውም ብሏል።
የሁለተኛው ምስክር ኮንስታብል ታምራት ዱላ ቃልም ተመሳሳይ ነበር። አማርኛ ቋንቋ አጥርቶ መናገር ባለመቻሉ የሚለው አይሰማም፣ በጣም እየፈጠነ የሚናገር በመሆኑም፣ ዳኛው “እንደው አስተርጓሚ የሚፈልግ ዓይነት ነገር እኮ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠበቃውና ዓቃቤ ሕጉም ሲጠይቁ ዳኛው በመካከል እየገቡ ይጠይቁ፣ እንዲብራራም ያደርጉ ነበር። ይሄ ምስክር በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት፣ ግንብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጥበቃ ሥራ እየሠራ እያለ፣ አንድ አረንጓዴ መኪና በሁለት ላዳ ታክሲዎች መካከል በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረች ስትመጣ፣ ፊሽካ ነፍቶ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ለማድረግ እንደሞከረ ገልጾ፤ ትንሽ ቆይቶ ጓደኛው ከሼራተን አካባቢ፣ በእጁ “ና! ና!” ብሎ እንደጠራውና፣ ስለተፈጸመው እንደነገረው፣ ከዛም ወደ ልጁ ሲሄዱ የልጁ ሕይወት እንደነበር፣ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ መጥፋቱን ገልጾ፣ ለፖሊስ ደውሎ እንደተናገረ መስክሯል። ስለሟች የአለባበሱንና የኑሮውን ሁኔታ እንዲናገር ሲጠየቅ፣ እዛ አካባቢ ለረጅም ጊዜ መሥራቱንና፣ ልጁ የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን ገልጾ፣ መጠጥ እየጠጣ ሲወድቅ እንደሚያውቀው ተናግሯል።
ሦስተኛ ምስክር ሆነው የቀረቡት የፕላን ምስክር ሲሆኑ፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ በቦታው ተገኝተው ፕላን ማንሳታቸውን ተናግረዋል፣ ስለ ፕላኑም አስረድተዋል።
ባነሱት ፕላን ላይ ስለተፃፈው ነገር፣ ከጠበቃው መስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የታርጋ ቁጥሩን መዝግቤያለሁ ያሉት አንደኛው ምስክር፣ ፕላኑ ሲነሳ በቦታው መኖራቸውን አረጋግጠው ፈርመው እያለ፣ በዚሁ ፕላን ላይ ፕላን አንሺው ደግሞ “ፕላኑን ተመልከቼዋለሁ የሰሌዳ ቁጥሩ ያልታወቀ ተሽከርካሪ ሰው ገጭቶና ገድሎ ያመለጠ ስለሆነ፣ በማስረጃ ጭምር በአስቸኳይ ይጣራ” ብለው ጽፈዋል። በወቅቱም የሰሌዳ ቁጥር የያዘ የዓይን ምስክር ካለ፣ ለምን ይሄ ተፃፈ? በሚል ጥያቄ አቅርቧል። እንደ አሠራር የታርጋ ቁጥር የሚያሠፍሩት ገጭቶ ያላመለጠና ሹፌሩ እዛው ኖሮ በፕላኑ ላይ ሲፈርም እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠበቃው ከእኝህ ምስክር ጋር ስለሟች አወዳደቅ፣ ስለ መኪናው አገጫጭ፣ በርካታ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ስለ ግጭቱም ከኮንስታብሎቹ ጠይቄ የተረዳሁት ነው ያሉትን ፕላን አንሺው ሲገልጹ “ሟች ከጓደኛው ጋር እየተጓተተ አስፋልቱን በማቋረጥ ላይ እያለ ይወድቃል። በወደቀበት በዚያው ፍጥነት በመኪናው ተገጭቷል። ገጪው መኪናም ልጆቹ ሲያቋርጡ አይቷቸዋል” የሚል ነበር።
የምስክሮቹ ቃል፣ ከተሰማ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ አንዱን ምስክር በአድራሻው ስላላገኘው ምስክሩ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝለት ጠይቆ ተፈቅዶለታል።
ዓቃቤ ሕግ ያለው ማስረጃ፣ ምን እንደሚያስረዳለት አጠቃሎ እንዲያቀርብ ዳኛው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ ጠበቃው ከጊዜ አንፃር ምላሻቸውን እዛው ለመስጠት ተዘጋጅተው መምጣታቸውን በመግለጽ የተከራከሩ ቢሆንም፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ዓቃቤ ሕግ በጽሑፍ አጠቃሎ የሚያቀርበውን የማስረጃ ዝርዝር ሂደት ለመጠባበቅ ለግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. ተቀጥሯል።
ሦስቱም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የመረበሽ፣ የመደናገጥ፣ የመርበትበትና የመንተባተብ ሁኔታ ይታይባቸው የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዴም ይሰጡት የነበረው ምስክርነት እርስ በእርሱ ይጋጭ ነበር። በተለይ ደግሞ ፖሊሶች ከመሆናቸው አንጻር ሁኔታቸው በችሎት የነበረው ተመልካች የምስክሮች ቃል በሚሰማበት ወቅት፣ ምስክሮች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ በሚፈጥርባቸው ስሜት፣ የማጉረምረም ድምፅ ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ከዳኛም፣ ከፖሊስም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ቴዲ ችሎቱ ተጠናቆ ከአዳራሹ ሲወጣ "ቴዲዬ እንወድሃለን" የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል። ከአዳራሹ ውጪም በርካታ ሰዎች ተሰብስበው “ምን ተባለ?” በሚል ከአዳራሹ የሚወጣውን ሰው ሲጠይቁ የታየ ሲሆን እንደሌላው ጊዜ በጩኸት ድጋፋቸውን ሲገልጹ አልታዩም።
ቴዲ አፍሮ በቀረበበት ክስ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ከዋለና፣ ቃሊቲ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ከታሰረ ጀምሮ እስከ ዛሬ (ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም.) አንድ ወር ከስምንት ቀናት ተቆጥረዋል።



