ለዓለም ደቻሳ

በግዜው በቀለ ጃለታ (ሜኖሰታ)

 

ይች ዓለም ጠፋች

የደቻስዋ ጉብል ተገፋች

የኢትዮጵያ አርኮማዋ ተወገደች

ተለማምጣ በነነች

ተንሰቅስቃ ተነነች

 

 

በከብት አገር ተወልዳ

ከአራዊት ጋር ተለማምዳ

ከእንስሶች መንደር ተወግዳ

 

እንቆቅልሿ ይች ዓለም

የት እንደገባች አናውቅም

ፀሀይ በቃ አታገኝም

ጨለመባት የኛው ኑሮ፤ የዚህ ዓለም

 

ተንከራታ ሳትደሰት

ተነቅላ ከዕትብተ መሬት

ከሰፊው አፈር ግባት

ወገኖቿ ሳይጠይቋት

አዘገመች ወደ አቀበት

የሊባኖስ ፍሬ ቅስፈት

ነጎደች ወደ ማይደረስበት

ሥር ሰደደች ወዲያው ጠወለገች የኛ አትክልት

 

ከአድማስ ማዶ ሰው ካለባት

ከቅዱሳን ከአዕላፍት

ከንጹሓን ከመላዕክት

ልትኖር ይሆን በአንድነት

ይሆን ይሆን ይች እመቤት

 

ወይስ …

የእሷ ምኞት

የእሷ ቅዠት

የህልም እዣት

 

ከአገር ማዶ ባሻገር

ወይ አልኖረች በኛው ሸገር

ልመናዋ ለመጥፋት ነው ላለመኖር

ወደ ምርጡ ለመንደርደር

 

ከእንባችን ጋር ትዘክር

የእሷ አይደለም፤ የኛው ነው ይህ ተዝካር

 

በቁም ቁመታችን

ህያው ሳለ ቁመናችን

ያሳየናል፤ ይታየናል መሞታችን

በቁልቅለት መውረዳችን

መልክ ማግኛ፤ መስታወት ነው ምሥላችን

ተከተፈ ወገናችን

ስለያዘን ጠላታችን

ሄደችብን ውዳችን

 

የስቃዩ፤ መመሳሰል አንድነቱ

እዚያም እዚህ፤ ተመሳሳይ በሁለቱ

ስለገባት ከጥንቱ

መመለሱን፤ ጠላችው የኑሮው ክፋቱ

ሁሉን ጣለች ቢፍቱ

 

እነ ጊፍቲ እነ ቡልቱ

እንግዲህ፤ እነሱም ሀሁ ይበሉ ይንገላቱ

 

ለመኖር ይዋቱ

ይታገሉ ከእንስሳቱ

ከለመዱን ከእንግልቱ

 

እንበላቸው ኑሩ በርቱ፤ ምናለበት አውሬዎቹ ቢሞቱ

የሰው ዘሮች እንዲኖሩ እንዲፈቱ!


በግዜው በቀለ ጃለታ ሜኖሰታ

 

3/16/2012 (መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ