በቤይሩት ስቃይ የደረሰባት ወጣት ኢትዮጵያዊት ሞተች
አንዳንዶች ”ራሷን አጠፋች” የተባለው ለሽፋን ነው ይላሉ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም. March 14, 2012)፦ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንጽላ ፊት ለፊት በሊባኖሳውያኑ ዓሊ ማህፉዝና ግብረአበሮቹ ፀጉሯንና ክንዷን በመጎተት እያሰቃዩ በመኪና አፍነው የወሰዷት የ33 ዓመትዋ ወጣት ዓለም ደቻሳ ዛሬ ጠዋት ራስዋን እንዳጠፋች ተገለጸ።
የቤይሩት መገናኛ ብዙኀን ወጣትዋ ኢትዮጵያዊት ዓለም ደቻሳ ዛሬ ንጋት ላይ ከምሽቱ 11 ሰዓት እስከ 12 ባለው ሰዓት ላይ ተኝታበት በነበረው ሆስፒታል ውስጥ በአንሶላዋ አንገትዋን አንቃ ራስዋን እንዳጠፋች ዘግበዋል።
ዴይሊ ስታር ያናገራቸው በቤይሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ቆንስላ አሳምነው ደበሌ ቦናሳ ወጣትዋ ኢትዮጵያዊ ራስዋን ማጥፋትዋን ዶክተሮች ደውለው እንደነገሯቸው ገልጸዋል። ቆንስላ አሳምነው ባለፈው ቅዳሜ ወጣት ዓለም ደቻሳን ጎብኝተዋት እንደነበርና በመልካም ሁኔታ ላይ ትገኝ እንደነበር ገልጸው፤ ዛሬ ንጋት 11 ሰዓት ላይ ዶክተሮቹ ሲጎበኝዋት በሕይወት እንደነበረችና ተመልሰው 12 ሰዓት ሲጎበኝዋት ግን ሕይወቷን አጥፍታ እንዳገኝዋት ዶክተሮቹ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
አንዳንድ ወገኖች ወጣት ዓለም ”ራሷን አጠፋች” የሚባለውን የማይቀበሉት ሲሆን፣ በዓሊ ማህፉዝና ግብረአበሮቹ መሰቃየቷንንና መታፈኗን የሚያሳየው ቪዲዮ በዓለም ከተሰራጨ በኋላ ከተለያዩ የሰብዓዊና የሴቶች መብት ተከራካሪ ወገኖች፣ ከመንግሥታትና ከበርካታ የዓለም ህዝብ ክፍል ቁጣን በማስከተሉ፤ ወጣት ዓለም የደረሰባትን በደል ለዓለም ይፋ እንዳታደርግ ሆን ተብሎ የተደረገ የሽፋን ሥራ ነው በማለት እየተከራከሩ ይገኛሉ።
ለወጣት ዓለም ደቻሳ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል መጽናናትን ይመኛል።



