ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅና ኃይሌ ገብረሥላሴ ቴዲ አፍሮን አነጋገሩት
ቴዲ አፍሮ በሽምግልና ሊለቀቅ ይችላል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. June 3, 2008)፦ ቅንጅቶችን በማስፈታት ሂደት ከፍተኛውን የሽምግልና ሂደት ያከናወኑት የሽማግሌዎች ሕብረት መሪና አባል የሆኑት ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ እና ዝነኛው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ባለፈው ዓርብ በቃሊቲ እስር ቤት በመገኘት ቴዲ አፍሮን ያነጋገሩት መሆኑን ታማኝ የሆኑት የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
ፕሮፌሰሩ ከአዲስ አበባ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ከዝነኛው አቀንቃኝ ቴዲ አፍሮ ጋር ከአሁን በፊት የቅንጅት እስረኞችን ለማስፈታት ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ቀጠሮ ተይዞላቸው ከኃይሌ ገ/ሥላሴ ጋር በመሆን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ የተነጋገሩት ዝርዝር ሁኔታ ምንነት እስካሁን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ያልተሳካልን ቢሆንም፤ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ ሙከራ እየተደረገ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ በርካታ ሁኔታዎች መኖራቸው ታውቋል።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ሙከራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ጠቅላላ የሽማግሌዎቹ ሕብረት በሰባሳቢው ፕ/ር ኤፍሬም አማካኝነት ምስጢራዊው ድርድር መጀመሩን ለማወቅ ችለናል።
ይህ ድርድር ድምጻዊው ያልፈጸመውን ወንጀል ፈጽሜያለሁ ብሎ እንዲወጣ የሚያስገድድ ከሆነ በቴዲ አፍሮ የወደፊት ሕይወትም ሆነ ማንነት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ሊጥል እንደሚችል አንዳንድ ለሁኔታው ቅርበት ያላቸው ታዛቢዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ጉዳይ በሚመለከት አስተያታቸውን እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው ወጣት የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት "ይቅርታ እያስጠየቁ ፍትህን ማጓደል ኢህአዴግ በቀጥታና በፍትሃዊ መንገድ ማድረግ የሚሳነውን ነገር በተዘዋዋሪና በእጅ አዙር መንገድ እነ ፕ/ር ይስኃቅ እያሳኩለት ነው።" ካሉ በኋላ፤ "በሌላ አነጋገር የሽምግልናን ካባ የደረቡ የኢህአዴግ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ያሰኛቸዋል።" ብለዋል። "ይሄ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችንና ባላንጣዎቹን እጅ የሚያሰጥበትና በወታደሮች ብቻ ሳይሆን በሽማግሌዎችና በታዋቂ ግለሰቦች እርዳታ ሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥንቅጥ የሚያዳፍንበት እንዲሁም ሌሎችንም በፍርሃት የሚሸብብበት የኢህአዴግ ልዩ መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኗል።" ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።
ሌላ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት ደግሞ "በሽምግልናው ሕብረት አማካኝነት የአቶ አሰፋ አብርሃ እና አቶ ታምራት ላይኔን ጨምሮ የኦነግና የቤተክህነት እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ታዋቂ ሰዎችና የአርቲስቶች ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሂደቱ የጠራና ጠቅላላ ብሔራዊ እርቅን ያዘለ ሆኖ እንዲቀጥል ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሽምግልናው ሕብረት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የሽምግልናውን ሂደትም በጥንቃቄ ሊያዩት ይገባል" ብለዋል።



