ችሎቱ እንደተለመደው በህዝብ ተጨናንቋል

የችሎቱ ሂደት በባለሙያዎች እየተተቸ ነው

Teddy Afro

Ethiopia Zare (ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. June 4, 2008)፦ዛሬ የተሰየመውና ቴዲ አፍሮ የተከሰሰበት ችሎት ብዛት ያለው ህዝብ የተከታተለው ሲሆን፣ 3 ሰዓት ከ30 ላይ የተሰየመው ችሎት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም የዓቃቤ ሕጉን የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ እንዲያቀርብ ከጠየቁ በኋላ መጀመሩን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።

 

ዓቃቤ ሕጉም ያቀረባቸው ስድስት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ ምን እንደሚያስረዱለት ያቀረበ ሲሆን፣ አንደኛ የአደጋ ቦታ ፕላን ሲሆን፣ ተከሳሽ የሚያሽከረክረው መኪና በቤተ መንግሥት አካባቢ ከላይ ሲመጣ ሟች ደጉ ይበልጣልን ከሩቁ ማየት ስለሚችል ከአደጋው ማትረፍ ይቻለው የነበረ ቢሆንም ሳያተርፈው መቅረቱን ያስረዳልኛል በማለት ያቀረበ ሲሆን፤ የተቀሩት አምስቱ ደግሞ መኪናውን የሚያሳይ ፎቶግራፍ (በትራፊክ ቢሮ አካባቢ)፤ ከምንሊክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ የም/ወረቀት (ኦሪጅናል ያልሆነናና የመርማሪው ስም ኢሳያስ ብቻ ተብሎ በእጅ የተጻፈበትና የዶክተር ፊርማ ያላረፈበት)፤ አስከሬኑ ቀና ተደርጎ የተነሳ ፎቶግራፍ፤ መኪናው አደጋ ከማድረሱ በፊት ምንም አይነት የቴክኒክ ብልሽት ያልነበረው መሆኑን አስረድቷል።

 

ዓቃቤ ሕግ አራት የሰው ምስክሮች አሉ በማለት ያቀረበ ከመሆኑም በላይ፤ አንዱ አደጋው ከተፈጸመ በኋላ የደረሰ ሲሆን፤ ሁለቱ የዓይን ምስክሮች ናቸው። አራተኛው ምስክር ሊገኝ ስላልቻለ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ብቻ የተያዘ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃም በተራው ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የማስረጃ ዝርዝር መግለጫዎች ተቃውሟል። ጠበቃው፤ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሽ በጎማ ሄዶበታል የሚል ሲሆን፣ የሟች አስከሬን የተገኘው ሰውነቱ ተቀጥቅጦና ተሰባብሮ ነው በማለት ተቃውሞውን ያቀረበ ሲሆን፣ እስከዛሬ በፍርድ ቤቶች ሕግ መሰረት የአስከሬን ምርመራ በሁለት ዶክተሮች ተመርምሮና ተፈርሞበት መቅረብ የሚገባው ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ውጤት በአንድ ኢሳያስ ተብሎ በቀረበ ኦሪጅናል ባልሆነ የምስክር ወረቀት መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን አመላክቷል።

 

በተጨማሪም የቀረበው የፕላን ማስረጃ ያልታወቀ መኪና ገጭቶ ማምለጡን ከመግለጹ ውጭ የተከሳሽ መኪና ወይንም ተከሳሹ ገጭቶ ማምለጡን የማይገልጽ ሲሆን፣ የመኪናውን አይነትና ታርጋ ቁጥር ያልታወቀ መሆኑን ከማስረዳት ያለፈ የተከሳሽ መኪና ስለመግጨቱ የቀረበ የፕላን ማስረጃ ባለመኖሩ ደንበኛዬን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነገር ስለሌለ በነፃ ይሰናበትልኝ በማለት ጠይቋል።

 

ዳኛውም "ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ወረቀት ይቅረብ" ሲሉ፣ የተከሳሽ ጠበቃ "ዓቃቤ ሕግ የለኝም ብሏል ባለው ውሳኔ ይሰጥ" ብሎ ሊያስረዳ ቢሞክርም፤ ዳኛ ልዑል "ጠበቃ ስነሥርዓት! አንዴ ትዕዛዝ ተሰጥቷል" በማለት ከገሰጹ በኋላ፤ "አሰራር ነው" በማለት ተከሳሽ ቴዲ አፍሮ መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ እንዲሰናበት ወይንም ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥለው ስለሆነ ይከላከል የሚል ብይን ለመስጠት ለዛሬ ወር ማለትም ለሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. በመቅጠር ችሎቱ የተበተነ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

 

የዛሬውን የችሎት ሂደት የተከታተሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሕግ ባለሙያ "በኢትዮጵያ ውስጥ የፍትህ ሂደትን መዝቀጥ በተለይ በወጣቶቹ የሕግ ሰዎች ዳንኤልና ነፃነት ላይ እና በድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ላይ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው የችሎት ትርዒት በግልጽ ያሳያል" ካሉ በኋላ፤ "በሕግ ሥርዓት ሂደት አንድ ዳኛ ዓቃቤ ሕግን ቻሌንጅ ማድረግ ሲገባው የለም የተባለን ኦሪጅናል የም/ወረቀት ወልዳችሁ አምጡ ማለት ዳኞቻችን በህሊናቸው ቅንጣት ታህል የማይታዘዙ መሆናቸውን በግልጽ ያስረዳል" ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ