ሁለቱ ጋዜጠኞች ክስ ሳይመሰረትባቸው ተፈቱ
Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 14 ቀን 2001 ዓ.ም. October 24, 2008)፦ ከረቡዕ ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር የነበሩት ጋዜጠኛ ሀብቴ ታደሰ እና ጋዜጠኞ አጥናፉ አለማየሁ ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው ዛሬ ማምሻውን መለቀቃቸውን ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ዘገበ።
የእንቢልታ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ሀብቴ ታደሰ እና የጋዜጣው አዘጋጅ አጥናፉ አለማየሁ ምንም እንኳን ረቡዕ ዕለት ጠዋት ከጋዜጣው አሣታሚና ዋና አዘጋጅ ጽዮን ግርማ ጋር ቃላቸውን ለፖሊስ ሰጥተው፣ ከሰዓት በኋላ ልደታ ወደሚገኘው ፍርድ ቤት ተወስደው ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
በማግስቱ ኀሙስ ዕለትም ችሎት ቀርበው የነበረ ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ በዋና አዘጋጅዋ ላይ ብቻ ክስ በመመስረት፣ በጋዜጠኛ ሀብቴ እና በጋዜጠኛ አጥናፉ ላይ ክሴን አላጠናቀቅሁም በማለቱ ሁለቱ ጋዜጠኞች በእስር እንዲቆዩ ተደርጓል።
ሲ.ፒ.ጄ. (CPJ - Committe to Protect Journalists) የተሰኘው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሁለቱን ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቅቋቸውና፤ በዋና አዘጋጅዋ ላይ የተመሰረተውን የማይረባ ክስ ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቋል። ሲ.ፒ.ጄ. ያወጣውን ማሳሰቢያ አዘል ዜና እዚህ በመጫን ያገኙታል።



