የቴዲ አፍሮን ችሎት የሚያዩትን ዳኛ ስም የተሳሳቱ ሦስት ጋዜጠኞች ታሰሩ
ጋዜጠኞቹ የእንቢልታ አሣታሚና ዋና አዘጋጅ፣ ምክትል ዋና አዘጋጅ እና አዘጋጅ ናቸው
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. October 22, 2008)፦ እንቢልታ ጋዜጣ የቴዲ አፍሮን ዘገባ በጋዜጣው ላይ ሲያስነብብ የዳኛውን የአባት ስም በመሳሳቱ የጋዜጣው አሣታሚና ዋና አዘጋጅ ጽዮን ግርማ፣ ምክትል አዘጋጁ ሀብቴ ታደሰ እና አዘጋጁ አጥናፉ ዓለማየሁ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን በእስር ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
ጋዜጠኞቹ ትናንት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተደውሎላቸው ለዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በተሰጣቸው መሠረት ፖሊስ ጣቢያ ሄደዋል። እዚያም ለፖሊስ ቃላቸውን እንደሚሰጡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የዋስትና መብት ይፈቀድላቸው አይፈቀድላቸው ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የታወቀ ነገር የለም።
በአሁኑ ሰዓት በሀገር ውስጥ ከሚታተሙ ጋዜጦች ውስጥ በብቸኝነት የሴት አሣታሚና ዋና አዘጋጅ ያለው እንቢልታ ጋዜጣ ሲሆን፣ አሣታሚዋና ዋና አዘጋጅዋ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት በፎርቹን የእንግሊዝኛ ጋዜጣ፣ በሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ እንዲሁም በኤቢቢአይ ዊክሊ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ ሠርታለች።
ምክትል አዘጋጁ ጋዜጠኛ ሀብቴ ታደሰም እንደዚሁ በሀገር ውስጥ በሚታተሙ ከስድስት በላይ ጋዜጦች ላይ እስከ አዘጋጅነት ሠርቷል። እንዲሁም ”ኔቸር” የተሰኘ በኢንቫይሮመንት ላይ የሚያተኩር የራሱን ጋዜጣ ያሳትም ነበር።
አዘጋጁ ጋዜጠኛ አጥናፉ ዓለማየሁ ደግሞ ከአሥራ አራት ዓመት በላይ በጦማር እና በጦቢያ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነትና በምክትል አዘጋጅነት ሠርቷል።



