Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. October 26, 2008)፦ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥረት የማዕዘን ደንጋይ የሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በ1998 ዓ.ም. የጀመሩት ውይይት ተቋርጦ “ገዢው ፓርቲ ራሱን ብቻ ለመጪው ምርጫ እያዘጋጀ ነው” ሲል መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ አስታወቀ።

 

መድረኩ ይህን ያስታወቀው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጽሕፈት ቤት ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን፣ በመግለጫው “በሀገራችን ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በውጭም በሀገር ውስጥም ከሚንቀሳቀሱት ከሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት የሚካሄድበት ሁኔታ ይመቻቻል፤ እንደዚሁም በ2002 ዓ.ም. ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ድጐማ የሚያገኙበት፣ የተዘጉ ጽ/ቤቶቻቸው የሚከፈቱበት እና የታሰሩ አባሎቻቸው የሚፈቱበት እርምጃ ይወስዳል” የሚል በፕሬዝዳንቱ ንግግር ውስጥ እንዲካተት ያቀረብነው ሃሳብ ለውይይት እንኳን እንዳይቀርብ በምክትል አፈጉባዔዋ ውድቅ ሆኖብናል ሲሉ በመግለጫው አስታውቀዋል።

 

በሀገራችን በአስከፊ ሁኔታ በገጠርም በከተማም እየደረሰ ስላለው ረሃብ የሚያወላዳ መፍትሔ የሚገኝበት ሁኔታ ይመቻቻል፣ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ በአስቸኳይ ስለሚወጣበት ሁኔታ አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ የሚወሰድ ይሆናል።

 

በጋዜጣዊ መግለጫው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከኦፌዴን፣ ከሶማሌ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ኃይሎች ቅንጅት አቶ አለን ናስር፣ በግል ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሲገኙ የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ተወካዮች አልተገኙም።

 

የዓረና ተወካዮች እነ አቶ ስዬ አብርሃ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያልተገኙት ባጋጠማቸው ኀዘን መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ፤ መግለጫው እነሱም የተስማሙበት የምክክር መድረኩ አቋም ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ እንዳረጋገጠው ከሆነ የአቶ ስዬ አብርሃ እናት ባለፈው ሣምንት ያረፉ ሲሆን፣ የቀብር ሥነሥርዓታቸው በተንቤን ተፈጽሟል።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ