ስድስት ምሁራን የውይይት ጽሑፋቸውን አቅርበዋል

Ethiopia Zare (እሁድ ታህሳስ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. December 28, 2008)፦ መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ (የምክክር መድረክ) ቅዳሜ ዕለት በኢምፔሪያል ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት ዝግጅት ላይ ስድስት ምሁራን የውይይት ጽሑፍ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ዘገበ።

 

ይህ በአዲስ አበባ የተካሄደው ስብሰባ ከሰዓት በኋላ ከ7፡30 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡00 ድረስ የዘለቀ ሲሆን፣ እጅግ በርካታ ሰዎች መገኘታቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

የመጀመሪያውንና “የኢህአዲግ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ችግሮቹ” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ገብሩ አስራት እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው።

 

ሁለተኛውንና “የብሔርና የግለሰብ መብት ጥያቄ በኢትዮጵያ - ትናንትና ዛሬ” በሚል ርዕስ ደግሞ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ ጥላሁን እንደሻው ነበሩ።

 

“የፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት ጥያቄ በኢትዮጵያ - ትናንትና ዛሬ” በሚል ርዕስ ሦስተኛውን ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ስዬ አብርሃ እና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እንደነበሩ ለመረዳት ችለናል።

 

ጽሑፎቹ ከቀረቡ በኋላ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት የተደረጉባቸው ሲሆን፣ ውይይቱ የተሳካና በጥሩ ሁኔታ የተከናወነ እንደነበር ለመረዳት ችለናል። የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የስብሰባው ተሳታፊዎች በውይይቱ መደሰታቸውንና ከፍተኛ ግንዛቤ ያስጨበጠ እንደነበር ገልፀዋል።

 

መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ (የምክክር መድረክ) በተለይም በሚቀጥለው ዓመት 2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በፊት ተከታታይና ሌሎች ተመሳሳይ ውይይቶችን እንደሚያደርግ ታውቋል። በሚቀጥለው ሣምንት ቅዳሜ ታህሳስ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ተመሳሳይ ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ችለናል።

 

የምክክር መድረኩ የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ሰኔ 17 ቀን እንደሆነና መስራቾቹም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዲኃሕ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን)፣ የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ሶዲኃቅ)፣ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና) የተሰኙት በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር በመሆን እንደሆነ ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ