Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. August 29, 2008)፦ ከ14 ሚሊየን ህዝብ በላይ በረሃብ እየተገረፈና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክልሎችም በድንበርና በመሬት ይገባኛል ጉዳዮች፣ በርካታ ዜጎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ መግባታቸው፣ የመንግሥትን ሀገር የማስተዳደር ብቃት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ አስታወቀ።

 

የምክክር መድረኩ ነኀሴ 20 ቀን 2000 ዓ.ም. በኢዴኃሕ ጽሕፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በብዙ የሀገሪቱ ክልሎች ረሃቡ ህዝቡን ከቀየው እያፈናቀለና በርካታ ወገኖችም በወቅቱ የድረሱልን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መድረክ መነፈጋቸውን ገልጧል።

 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምን ያህል ረሃብተኞች እንዳሉ ትክክለኛ መረጃ ይኖራቸው ዘንድ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ መልስ የሰጡት ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ ምን ያህል ረሃብተኞች፣ በየት አካባቢ እንዳሉ ማረጋገጥ የሚገባው መንግሥት እንደሆነ ገልጠው፣ ያም ሆኖ ባሉት መረጃዎች ከ14 ሚሊዮን ህዝብ በላይ መሆኑንና በየጊዜውም ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

አቶ ገብሩ አሥራት በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ መንግሥት የሰጠው አኀዝ ቢወሰድ እንኳ የረሃቡ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አውስተው “15 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል በሚባለው በትግራይ ክልል ረሃቡ ሰውንና እንስሳትን እየጎዳ ነው፣ በሚሊኒየሙ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ እናሳይ በሚል መንግሥታዊ አቋም ችግሮች እየተድበሰበሱ ነው” ብለዋል።

 

በኦብኮ የፓርላማ አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በተጨማሪ እንደተናገሩት በምሥራቅ ወለጋ ኖኖ፣ አርጆ፣ ምዕራብ ሸዋ ባኮ፣ ዳንዲ፣ እልፈታ፣ ሚዳቅ በአርሲ ደግሞ ኮፈሌ፣ ቆሬና ጉጂ ህዝቡ በረሃብ ምክንያት ወደ ከተማ እየፈለሰ መሆኑንና በረሃቡ ላይ ፖለቲካ እንዳጠላ ተናግረዋል።

 

መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ በጋዜጣዊው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ እስካሁን ድረስ ባካሄዳቸው ውይይቶች የጋራ መግባቢያ ሰነዶች ከማዘጋጀት ጀምሮ ህዝባዊ ውይይት ለማካሄድ የሚስችሉትን ሃሳቦች መቅረጹን አስታውቋል።

 

መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ ሰኔ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. በኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን)፣ በሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ሶዲኃቅ)፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዴኃሕ) እና በዓረና ትግራይ ንዲሞክራሲን ንሉዓላዊነት መመሥረቱ ይታወሳል። በቅርቡ ሕጋዊ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ያገኘው የአንድነት ፓርቲ ምክክሩን ሊቀላለቀል እንደሚችል ይገመታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ