ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተለዋጭ ቤት በኪራይ ሊሰጣቸው ነው
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሰኔ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. July 3, 2008)፦ በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ የመኖሪያ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸው የነበረው የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተለዋጭ ቤት በኪራይ መልክ ሊሰጣቸው እንደሆነ አስታወቁ።
ለተወካዮች ም/ቤት በደብዳቤ ጥሪያቸውን አቅርበው የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአቶ ብርሃኑ አዴሎ በደብዳቤ እንዲጠይቁ በገለጹላቸው መሠረት፣ በዚያው ዕለት ለአቶ ብርሃኑ አዴሎ ደብዳቤ መፃፋቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፣ አቶ ብርሃኑም ተለዋጭ ቤት በኪራይ ይሰጠኝ ዘንድ አስታውቀውልኛል፤ በቅርቡም ተፈፃሚ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸውም ገልፀዋል።
ዶ/ር ነጋሶ፣ በእርሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ተጋርጦ የነበረው በሜዳ ላይ የመበተን አደጋ ለጊዜውም ቢሆን እንደተነሳላቸው የገለፁ ሲሆን፣ ችግሩ በተከሰተበት ወቅት ከጐናቸው የነበሩትን አመስግነዋል።
የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ቤታቸውን ሊለቁ ነው መባሉ የብዙ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት በመሳቡ ጉዳዩ በሀገር ቤት በሚታተሙ በ11 ጋዜጦች ላይ ሽፋን አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካ ድምፅ “VOA” ጉዳዩን አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን፣ አቶ ብርሃኑ ጀምበሬን እንዲሁም ራሳቸው ዶ/ር ነጋሶን በማነጋገር ሰፋ ያለ ዘገባ ሰርቶ እንደነበር ይታወሳል።
ዶ/ር ነጋሶ በችግራቸው ወቅት ከጎናቸው በመሆን የረዷቸውን በሙሉ፣ አንዳንድ የኢህአዴግ አካላትን ጨምሮ አመስግነው፣ በኪራይ መልክ የሚሰጣቸውን ቤት እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልፀዋል።