Ato Seye AbrhaDr. Negasso Gidadaጥያቄአቸው የፊታችን እሁድ በአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ ይታመናል

ዶ/ር ነጋሶ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠየቁ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ኅዳር 17 ቀን 2002 ዓ.ም. November 26, 2009)፦ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የህወሓት ታጋይና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስየ አብርሃ ዛሬ ኀሙስ ኅዳር 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ጠዋት በግዮን ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ገለጹ። የአባልነት ጥያቄአቸው የፊታችን እሁድ ኅዳር 20 በአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በ1987 ዓ.ም. “ሕገ-መንግሥቱ ዲሞክራሲያዊ ነው፣ ምርጫው ዲክራሲያዊ ነው፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የተሳተፉበት ነው፣ …” ሲሉ የኢህአዲግ አባል በነበሩበት ጊዜ ራሳቸው የተናገሩትን በማንሳት፤ ሙሉ ለሙሉ ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም በሕይወት ዘመናቸው ከሚያፍሩባቸውና ከሚያዝኑባቸው ሥራዎቻቸው አንዱ መሆኑን በመግለጸው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።

 

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የገዥውን ፓርቲ ኢህአዲግን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ፤ አቶ ስየ አብርሃም ከህወሓት ከተባረሩ በኋላ የተቀላቀሉት የፖለቲካ ፓርቲ እንዳልነበረ ይታወቃል። የአንድነት ፓርቲ አባላት ከዚህ ቀደም ሁለቱን ታዋቂ ግለሰቦች ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋቸው የነበረ ቢሆንም፤ ፓርቲውን ሳይቀላቀሉ መቆየታቸው ይታወቃል።

 

ሁለቱ ታዋቂ ግለሰቦች የመድረክ መስራች ሲሆኑ፤ ዶ/ር ነጋሶ ኦፌዲን (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን)፤ አቶ ስየ ደግሞ ዓረናን ይቀላቀላሉ ተብሎ ሲወራ ሰንብቶ ነበር።

 

ዶ/ር ነጋሶ አንድነትን ለመቀላቀል የወሰኑባቸውን ምክንያቶች ሲጠቅሱ፤ አንድነት ለግለሰቦች መብትና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚታገል በመሆኑ እንዲሁም የወ/ት ብርቱካን እስር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ወ/ት ብርቱካን ወንጀለኛ ሳትሆን የፖለቲካ እስረኛ ነች፤ ካሉ በኋላ ወ/ት ብርቱንን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የአቶ ስየ አብርሃን አንድነት ፓርቲን የመቀላቀል ጥያቄ የፊታችን እሁድ ኅዳር 20 በኢምፔሪያል ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂደው የአንድነት ፓርቲ ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል። ምንጮቻችን እንደጠቆሙት ከሆነ፤ ጠቅላላ ጉባዔው ግለሰቦቹን የፓርቲው አባላት አድርጎ እንደሚቀበላቸው ያላቸውን ግምት ገልፀዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ