ቴዲ አፍሮ ዛሬም አልተፈታም
የተጭበረበረ ሰነድ እንዲጣራ ለሣምንት ተቀጥሯል
ሁለት ጋዜጠኞች ታሰሩ
Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. July 4, 2008)፦ ዛሬ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን እንደሚፈታ በአዲስ አበባ ውስጥ ወሬ ሲናፈስ የሰነበተ ቢሆንም ብይኑ ለሣምንት ተቀጥሯል። በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ዶ/ር የተፈረመበት የሟች ደጉ ይበልጣል የሞት የምስክር ወረቀት ቴዲ ከተከሰሰበት ቀን ጋር ልዩነት በመፍጠሩ ዳኛው ዛሬ ብይን መስጠት ሲገባቸው እስኪጣራ ለሣምንት ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን መበተናቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
በዶክተር የተፈረመበትና ኦሪጅናሉ ሰነድ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/9 ዓ.ም. ሞቶ በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ተመርምሯል የሚል ሲሆን፣ ቴዎድሮስ የተከሰሰው በ23/2/99 ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሟቹን ገሎ አምልጧል የሚል ነው። ማስተካከያ ተብሎ የቀረበውና በሆስፒታሉ አስተዳደር በኩል የተላከው አዲሱ ማስረጃ ደግሞ ዶ/ሩ በስህተት ነው የላከው፤ ሟች የሞተው በ23/2/99 ሲሆን፣ የተመረመረው በ24/2/99 ነው የሚል መሆኑ የታወቀ ሲሆን የሕግ ባለሞያዎች የዶ/ሩን ማስረጃ ማንም ሊያስተካክለውም ሆነ ሊያሻሽለው አይገባም ስህተት ቢሆን እንኳ ከላይ ያለው ቀን እንጂ በሰነዱ ላይ የተጻፉት ቀናቶች በሙሉ አንድ አይነት ሊሆኑ አይችሉም ነበር የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የቴዲ ጠበቃም ደንበኛው የተከሰሰበት ቀንና ሟች የሞተበት ቀን ተመሳሳይ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ደንበኛው እንዲለቀቅለት ቢጠይቅም፤ ዳኛው "መመርመር አለበት" በማለት ለሣምንት ቀጠሮ ሰጥተው ችሎቱን መበተናቸውን ለማወቅ ችለናል።
ችሎቱ ዛሬም እንደወትሮው ብዛት ያለው ህዝብ ቢታይበትም የደህንነቱ ብዛትም የዛኑ ያህል እንደነበር እና ሁለት ጋዜጠኖች መታሰራቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የታሰሩት ሁለት ጋዜጠኞች አንዱ የአዲስ ነገር አዘጋጅ አብርሃም በጊዜው እና የቀድሞ አስኳል ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረችው ጽጌረዳ ኃይሉ የችሎቱን ሂደት ቀርጻችኋል በሚል ሰበብ ነው የታሰሩ። ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ በህዝብ ፊት በፌደራል ፖሊስ እንደተደበደበች የዓይን ምስክሮች ገልጸውልናል። በአሁኑ ሰዓት ጽጌረዳ የተለቀቀች ሲሆን፣ አብርሃም በጊዜው ግን በልደታ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሮ እንደሚገኝ ለመረዳት ችለናል።



