- የምኒልክ ሆስፒታል ኩባዊ አስክሬን መርማሪ ፍርድ ቤት በሰነዱ ላይ ምስክርነት ሰጡ

- ቴዲ አፍሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ምሬቱን ለፍርድ ቤቱ ገለፀ

- ቴዲ ሲናገር እናቱን ጨምሮ ሰዎች አለቀሱ

Teddy Afro

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. July 11, 2008)፦ በህዝብ ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ የሆነው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በቀረበበት ክስ ላይ ሁለት ዓይነት ቀን ያለው የሰነድ ማስረጃ ሰጥቷል የተባለው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በታዘዘው መሰረት የኩባ ዜግነት ያላቸው የአስክሬን መርማሪ ፍ/ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃል ሰጡ።

 

ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስቲያ በጽሕፈት ቤት በኩል ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ ሆስፒታሉ ሟች ደጉ ይበልጣልን በሚመለከት የሰጠው የአስክሬን ምርመራ ውጤት አከራካሪ ሆኖ በመገኘቱ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ወይም ሌላ ባለሙያ በዛሬው ዕለት በችሎት ተገኝተው ሰነዱን በሚመለከት እንዲያስረዳ በታዘዘው መሰረት ቀርበው አስረድተዋል።

 

ባለሙያው እንዲያስረዱ የተፈለገው ቴዲ አፍሮ ተጠርጥሮ በተከሰሰበት ሰው ገጭቶ የማምለጥ ወንጀል በዓቃቤ ሕግ ከቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች አንዱ የሟች ደጉ ይበልጣለ ከምኒልክ ሆስፒታል የተሰጠ የአስክሬን ምርመራ ውጤት በሁለት አይነት ቀን የተጻፈ ሁለት ማስረጃ ጽፎ በመስጠቱ ነው።

 

ይህ የምርመራ ውጤት ዓቃቤ ሕጉ ከክሱ መዝገብ ጋር አያይዞ ያቀረበ ሲሆን፣ ማስረጃው ከምኒልክ ሆስፒታል ከወጣም አንድ ዓመት ከሰባት ወር አስቆጥሯል።መጀመሪያ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ይኸው የሰነድ ማስረጃ በአስክሬን መርማሪው ዶ/ር የተፈረመ ዋናው (ኦርጂናሉ) ሳይሆን በተርጓሚ ፊርማ የወጣ ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ የተተረጎመ ሰነድ በመሆኑ፣ ኦርጂናል ሰነዱ እንዲመጣ በጠበቃው አማካይነት በቀረበ የመከራከሪያ ሃሣብ ዓቃቤ ሕግ ሰነዱን ለምን እንዳላቀረበ፣ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቅ ሪሶርስ ላለማባከን ስንል ነው። የሰጡንም የአማርኛውን ሰነድ ብቻ ነው በሚል መልስ ቢሰጥም ትርጉሙ የተሠራበት ዋናውን ሰነድ እንዲያቀርብ በመታዘዙ ባለፈው ሣምንት ዋናውን ሰነድ በጽ/ቤት በኩል አቅርቧል።

 

የቀረበው የእንግሊዘኛው ሟች መሞቱ የተረጋገጠበት ዋናው የምስክር ወረቀት፤ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ገብቶ በ23/2/99 ተመርምሮ ወጥቶአል የሚል ነው። የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ይህንኑ ሰነድ ተመልክተው በደንበኛዬ ላይ የቀረበው ክስ በ23/2/99 ዓ.ም ከለሊቱ 8 ሰዓት ገጭቶ አምልጧል የሚል በመሆኑ ማስረጃው ለተያዘው ጉዳይ እና ከቀረበው ማስረጃ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ደንበኛዬ በነፃ ሊሰናበት ይገባል ሲል የመከራከሪያ ሃሣብ ያቀረበ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ስህተት የተፈጠረው በሆስፒታሉ ምክንያት ነው እንጂ በዓቃቤ ሕግ ባለመሆኑ የተስተካከለ ሰነድ አመጣለሁ ባለው መሠረት ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተፃፈ ሌላ የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

 

ለሁለተኛ ጊዜ ያመጣው የሰነድ ማስረጃ ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያ እና ምርመራ መምሪያ በሸኚ ደብዳቤ የተላከ ሲሆን፣ ደብዳቤው "በ12/10/2000 ዓ.ም. በደብዳቤ ቁጥር 20307/ወ/መ/42 ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በ23/02/99 ዓ.ም. የአስክሬን ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን የሚገልፅ በቁጥር 856/44/99 በ04/03/99 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የላክንላችሁ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ማስተካከያ ተደርጎ እንዲላክላችሁ መጠየቃችሁ ይታወቃል።

 

"በመሆኑም ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. የተደረገላቸው መሆኑን እያረጋገጥን፣ ስህተቱ የተከሰተው በወቅቱ የነበሩት የአስክሬን መርማሪ ባለሙያ ወደ ዋናው መዝገብ በሚያሰፍሩበት ወቅት በተከሰተ ግድፈት መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።" የሚል ነው።

 

ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ የተላከው የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ወደ ምርመራ ክፍሉ ገብቶ በ24/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቷል የሚል ነው።

 

ፍ/ቤቱ ባለፈው ሣምንት በዋለው ችሎት የቴዲ አፍሮ ጠበቃና ዓቃቤ ሕጉን በሰነዱ ጉዳይ ላይ ያከራከረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ማስረጃውን የሰጠው የምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ቀርበው አስረድተዋል።

 

የኩባ ዜግነት እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት የአስክሬን መርማሪ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ባለሙያው መልስ ከመስጠታቸው በፊት የሚያቀርበው መቃወሚያ እንዳለው በመግለጽ ቢቃወምም ከዳኛው በደረሰው ከፍተኛ ተግሳጽ ባለሙያው መሃላ እንዲፈጽሙ ተብሏል።

 

ባለሙያው መሃላ እንዲፈጽሙ ሲታዘዝ ከምንሊክ ሆስፒታል በአስተርጓሚነት የመጡት ግለሰብ ክርስቲያን ስላልሆኑ መሃላ መፈጸም እንደማይችሉ ቢገልጹም ባለሙያው ግድ የለም መሃላውን እፈጽማለሁ በማለታቸው መሃላ እንዲፈጽሙ ተደርጓል።

 

ፍርድ ቤቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ በመጣ አስተርጓሚ ሥራውን ሰርቷል። ሌላ ጊዜ የውጭ ዜጋ ሲመጣ አስተርጓሚ ከፍርድ ቤቱ የሚመደብ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ግድ የለም ይተርጎም በሚል ስሜት በምኒሊክ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ውጤት በመተርጎም የሚታወቅ ግለሰብ ቀርቦ እንዲተረጉም ተደርጓል።

 

ባለሙያው እንግሊዘኛ መናገር አይችሉም በሚል በትርጉም እንዲያስረዱ የተደረገ ቢሆንም በሚመሰክሩበት ወቅት አስክሬን ሲመረምሩ ውጤቱን በእንግሊዘኛ እንደሚጽፉና እንደሚተረጎም አስረድተዋል።

 

ባለሙያው ስለ ሟች አስክሬን ሲጠየቁ አስክሬኑን የመረመሩት ሐኪም ሴት መሆናቸውንና አሁን አገር ውስጥ እንደሌሉ ገልጸው፣ አሁን በቦታው ላይ ያሉት ራሳቸው እንደመሆናቸው ጉዳዩን ማጣራታቸውን አስረድተዋል። የመጀመሪያዋ ሐኪም አስክሬኑን ሲመረምሩ ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስረጃ መጻፋቸውንና ይኸው ማስረጃ ወደ መዝገብ ሲገለበጥ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ገብቶ በ23/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቶአል ተብሎ መጻፉን መስክረዋል።

 

ማስረጃው ከመዝገቡ ላይ ተገልብጦ ለፖሊስ መሰጠቱን ከተናገሩ በኋላ ፖሊስ ይህንኑ ማስረጃ እንዲስተካከልለት ሲጠይቅ ከመጀመሪያዋ ሐኪም የእጅ ጽሑፍ ላይ አይተው ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስተካከያ እንደሰጡ ተናግረዋል።

 

ጠበቃው በፍርድ ቤቱ አማካኝነት ባለሙያው ጥያቄ እንዲጠየቁለት ካመለከተ በኋላ አንድ ሁለት ጥያቄዎችን እንደጠየቀ ከዳኛው ጋር ባለመስማማቱ ጥያቄው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ የምርጫ ቦርድ ጠበቃ ሲሆን፣ የቅንጀት አመራሮች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት እስሩን ደግፎ ሞት ሊፈረድባቸው ይገባል እያለ በመንግሥት ራዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በየቀኑ መግለጫ ሲሰጥ የነበረ ጠበቃ ነው።

 

ጠበቃው በዛሬው ዕለት በችሎት ያሳየው አቀራረብ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ደንበኛው በተከሰሰበት ጉዳይ ላይ ከማተኮር ይልቅ በማናለብኝነት ስሜት እልህ መግባባትን ነው። እንዲያውም "ደንበኛዬ በጠበቃ እንዲከራከር ካልፈለጋችሁ ትቼ መሄድ እችላለሁ እንጂ ሰብዓዊ መብቴን አትነፍጉኝም" እስከማለት ደርሷል።

 

ዓቃቤ ሕግ "ጠበቃው ፍርድ ቤቱንና ዓቃቤ ሕግን ዘልፏል፤ ስለዚህም እንከሳለን" ሲል የተደመጠ ሲሆን ሦስቱም አካላት በጋራ በመሆን የተጣሉ መስለው የቴዲ አፍሮን ጉዳይ ለማቀዛቀዝ ያሰቡ ይመስላሉ።

 

ቴዲ አፍሮ ለመናገር እንደሚፈልግ ገልጾ፣ ከተፈቀደለት በኋላ "የተከበረው ፍርድ ቤት ስለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ! እኔ የማምነው ይህን ሁሉ ሰው በሚያይ እግዚያብሔር ነው። ግን አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። ፍርድ ቤቱንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የምጠይቀው ጉዳዩን በሚገባ ተረድተው በነፃ እንዲሰናብቱኝ ነው።" ሲል ተደምጧል። በዚህን ሰዓት ወላጅ እናቱን ጨምሮ በርካታ ሰው ድምጹን አውጥቶ ሲያለቅስ ተሰምቷል። ዳኛው ጉዳዩን ገለልተኛ ሆነው በማየት ላይ መሆናቸውን አስረድተው የግራ ቀኙን ክርክር መርምረው ለሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በነፃ ይሰናበት ወይም ደግሞ ይከላከል የሚለውን ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ