Teddy Afroየታሰሩት “ችሎት ረብሻችኋል፣ ድንጋይ ወርውራችኋል” በሚል ነው

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. July 22, 2008)፦ በትናትናው ዕለት የቴዲ አፍሮን ችሎት ለመከታተል ከመጡ ችሎት ተከታታዮች መካከል አስሩ ታሰሩ። በዛሬው ዕለትም ፖሊስ ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት አምስቱን አቅርቧቸው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ፈቅዶለታል። 

 

በትናንትናው የቴዲ አፍሮ ችሎት ዳኛው ሥራቸውን ጨርሰውና ችሎት በትነው ከሄዱ በኋላ ቴዲ እጁን ወደላይ ቀስሮ ”እግዚያብሔር ያውቃል!” ሲል፤ አብዛኛው ሰው ”ቴዲዬ አይዞህ! እንወድሃለን!” ሲል የጮኸና ያለቀሰ ሲሆን፣ ወዲያውም ”ማንም ሰው ሳንፈቀድለት እንዳይወጣ” የሚል ትዕዛዝ በፖሊስ አዛዡ ስለተሰጠ ችሎቱን ሊከታተሉ የገቡት ሰዎች አምስት ደቂቃ ከችሎቱ ሳይወጡ ለመቀመጥ ተገድደዋል።

 

ከዚያም ”ውጡ” ሲባል የችሎቱ ታዳሚ መውጣት ይጀምራል። ወዲያውም ከችሎቱ ውስጥ ከወጡት ሰዎች ውስጥ አስሩ ሰዎች ተለቅመው ይወሰዳሉ። ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ በዲጂታል ቪዲዮ ይቀርጹ የነበሩት ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች የችሎቱ ታዳሚ እንዳይወጣ በታዘዘበትና በታገተበት 5 ደቂቃዎች ውስጥ የተቀረጸውን ቪዲዮ መልሰው በማየት ያለቀሱትንና ቴዲ አፍሮን የሚያበረታቱ ቃላት ተናግረዋል ብለው የገመቷቸውን ሰዎች ነው የያዙዋቸው።

 

ትናንት ችሎቱ ከተበተነ በኋላ የተያዙት እነዚህ አስር ሰዎች ወደ ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል። ሰዎቹ የተያዙበት ምክንያት ሁለት ሲሆን፣ አንደኛው ”ችሎት ረብሻችኋል”፤ ሁተኛው ደግሞ ”ድንጋይ ወርውራችኋል” በሚል መሆኑን እነዚሁ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ከአስሩ ሰዎች ውስጥ አምስቱ ከሰዓት በኋላ የተፈቱ ሲሆን፣ አምስቱ ግን በፖሊስ ጣቢያው ታስረው አድረው ዛሬ ፍርድ ቤት ፖሊስ አቅርቧቸው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።

 

ከታሰሩትና ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሰዎች ውስጥ የሚጥል (ኢፕሊፕሲ) በሽታ እንዳለባት የምትታወቀው ወ/ት ቅድስት በቀለ የተባለችና ምርጫ 97ን ተከትሎ ከቅንጅቱ አመራሮች ጋር ”ጎማ አቃጥለሻል” በሚል ሁለት ዓመት ታስራ የተፈታችው ግለሰብ እንደምትገኝበት እነዚሁ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል። ከወ/ት ቅድስት በተጨማሪ ሌሎች ሴቶችም መታሰራቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

በስፍራው የነበሩ የዓይን ምስክሮች ድንጋይ ሲወረወር እንዳላዩ ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጹ ሲሆን፤ ሰዎች ድምፃቸውን ማሰማት የጀመሩት ዳኛው ሥራቸውን ጨርሰው ችሎቱን ከበተኑና እሳቸውም ችሎቱን ጥለው ከወጡ በኋላ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

 

ችሎት ተገኝተው የነበሩ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የሕግ ባለሙያ ”ታሳሪዎቹ ችሎቱን ረብሸው ከሆነ መጠየቅ ያለባቸው በዛው ችሎት ነበር። ነገር ግን የተላቀሱትና ’ቴዲዬ እንወድሃለን!’ ሲሉ ድምፃቸውን አውጥተው የተናገሩት ችሎቱ ከተበተነ በኋላ ስለሆነና ዳኛው ባላዩትና ባልታወኩበት ረብሻ ’ችሎት ተረበሸ’ ብለው መቅጣት እንደማይችሉ ስለሚታወቅ ’ድንጋይ ወርውረዋል’ የሚል ቅጥያ ተጨምሮበት በሌላ ችሎት እንዲቀርቡ ተደረገ ” ሲሉ ሙያዊ ትንተናቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ