Teddy AfroEthiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. July 24, 2008)፦ ቴዲ አፍሮን ፖሊሶች ሲጎትቱት የሚያሳየውን ፎቶግራፍ (በግራ በኩል የሚታየውን ፎቶ) በፊት ገጹ ላይ ያወጣው በሀገር ውስጥ የሚታተመው ”መሰናዘሪያ” የተባለው ጋዜጣ በፎቶግራፉ ምክንያት መከሰሱን ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው መረጃ አስረዳ። የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ወሰንሰገድ መሸሻን ፖሊስ ጠርቶታል።

 

ዋና አዘጋጁ የፊታችን ዓርብ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲቀርብና ቃሉን እንዲሰጥ መጥሪያ እንደደረሰው ለመረዳት ችለናል። ”መሰናዘሪያ” ጋዜጣ በየሣምንቱ ሰኞ የሚታተም ጋዜጣ ነው።

 

ክሱ ”የፖሊሶቹን ፎቶ ፊት ለፊት አውጥታችኋል” የሚል እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

 

ባለፈው ሚያዝያ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. የዕንቁ መጽሔት በሽፋኑ ላይ የቴዲ አፍሮን ፎቶግራፍ በመያዙና በውስጡ ቴዲ አፍሮን በሚመለከት ጽሑፍ ስለነበረው ሕትመቱን አጠናቅቆ ከማተሚያ ቤት ሳይወጣና ሳይሰራጭ በፊት የመጽሔቱ አራት ባልደረቦችና የታተመው መጽሔት ጭምር ታስረው እንደነበር አይዘነጋም።

 

ከቴዲ አፍሮ ክስ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በርካታ ሰዎች እየታሰሩና እየተከሰሱ መሆኑ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበና ገረሜታን እየፈጠረ እንደሆነ ታውቋል። ብዙዎች የቴዲን ክስ ”ሰው ገጭቶ በመግደል” ከሚለው ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ያምኑ ዘንድ እያስገደዳቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ