Teddy AfroEthiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. July 26, 2008)፦ የቴዲ አፍሮን ጉዳይ በዳኝነት በመመልከት ላይ ያሉትን ዳኛ ልዑል ገብረማርያምን እና የምኒልክ ሆስፒታል አስተርጓሚ ሊከሰሱ ነው። ከሳሻቸው የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ሲሆን፣ በብይኑ ላይም ይግባኝ ሊል መሆኑን ለአዲስ ነገር ጋዜጣ ገለጸ። 

 

ጠበቃው አቶ ሚሊዮን "ዳግማዊ ምኒልክ አስከሬን የመረመረበትን ቀን መግለጹ ስህተተኛ ያደርገዋል። ምርመራው መቅረብ ያለበት የሞተበትን ቀን ነው" በማለት ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የቀረበውን የአስክሬን ምርመራ አስመልክቶ ገልጿል።

 

አቶ ሚሊዮን “ኩባዊው ዶክተር ላደስፔርቶ ሞያ በሰጡት ቃል ላይ፤ አስከሬኑ ጥቅምት 23 ቀን መግባቱን ከፖሊስ ወረቀት ላይ ማየታቸውን ነው የገለጹት። ይህ ደግሞ ሬሳው በዕለቱ መግባቱን አያሳይም፤ እንደውም አስከሬኑ ሆስፒታል ከገባ አንድ ቀን ወይም ሣምንት ሆኖታል ለማለት የሐኪም ምርመራ ያስፈልገዋል። ሐኪሙ የገለጹት አስከሬኑ ምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ሳይሆን፣ በፖሊስ ወረቀት ላይ ያዩትን ማስፈራቸውን ነው" በማለት ምርመራ የተደረገበትን ቀን መግለጹ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ጊዜ እንደማያሳይ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ቴዲ አፍሮ ስለመግጨቱ እና ስለመግደሉ አስረጂ አለመሆኑን ገልጿል።

 

የቴዲ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን "እነዚህ ሁሉ ስህተቶች ሲሠሩ ለፍርድ ቤቱ ተቃውሟችንን እንዳንገልጽ በዳኛው ተከልክለናል” ብሏል። "ፍርድ ቤቱ እንደ ከሳሽ ሆኖ የዓቃቤ ሕግን ሥራ ተክቶ ማስረጀ ቆጥሮብናል። ዳኛ ልዑል ገብረማርያምን ለዳኞች አስተዳደር በዲሲፕሊን እንከሳለን። በተጨማሪም የሕክምና ወረቀቱን የተረጐሙትን ባለሙያ በሥነ ምግባር ጉድለት በወንጀል ክስ እንመሰርትባቸዋለን” ሲል ገልጿል።

 

ከዚህም ሌላ የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. (July 21, 2008) በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ቴዲን “በተከሰሰበት ወንጀል ይከላከላል” በማለት በሰጠው ብይን ላይም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ የወያኔ ቀንደኛ ደጋፊና ምርጫ ቦርድ ጠበቃ ሲሆን፣ በምርጫ 97 በቅንጀት አመራሮችና ሌሎች ተቃማዊዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የውግዘት ጦርነት በመክፈት በየቀኑ በኢቲቪ መግለጫ ሲሰጥ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም።

 

ዳኛውም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለተኛ ወንጀል ችሎት ከባድ የሆኑ የወንጀል ጉዳዮችን የሚከታተሉ ዳኛ ሲሆኑ፣ የቅንጅት አመራሮች በተከሰሱበት ችሎት በቀኝ ዳኛነት ሲያስችሉ የነበሩ ናቸው። እኚሁ ዳኛ በድንገት ቀላል የሚባሉ የግጭት ጉዳዮች ወደሚታይበት 8ኛ ወንጀል ችሎት እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ የቴዲን ጉዳይ እንዲያዩ ተደርጓል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ