አንድ በቆሎ 2 ብር ገብቷል  

ባለፈው ዓመት 50 ሣንቲም የነበረው አንድ የተጠበሰ በቆሎ 2 ብር ከ50 ሣንቲም ገባ

Ethiopia Zare (እሁድ ሐምሌ 20 ቀን 2000 ዓ.ም. July 27, 2008)፦ በዘንድሮው የምርት ዘመን የበቆሎ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በማጠሩ የአንድ ነጠላ የተጠበሰ በቆሎ ዋጋ ሁለት ብር ከ50 ሣንቲም ሲሆን፣ ያልተጠበሰው ደግሞ ሁለት ብር እየተሸጠ መሆኑን በአዲስ አበባ ተዘዋውረው ያረጋገጡ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ። ባለፈው ዓመት ሦስቱ የተጠበሰ በቆሎ አንድ ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አንድ ፍሬ በቆሎ ደግሞ 50 ሣንቲም ነበር።

 

በተለይ በክረምት ወቅት መንገዶች በበቆሎ ይጨናነቁ እንደነበርና በመንገዶች ዳር ላይ በከሰል ፍም አስጠብሶ ወደ ቤት መግባትም ሆነ በመንገድ ላይ የተጠበሰ በቆሎ እየበሉ መጓዝ የተለመደ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት ግን የበቆሎ ዋጋ እጅግ ከመናሩ የተነሳ በመንገድ ላይ የሚታየውም በጣም በጥቂት አካባቢዎች መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

የ2000 ዓ.ም. ክረምት የበቆሎ ሸማች የሆነውን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል "በቆሎ ድሮ ቀረ" አሰኝቶታል። በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰው መንገድ ላይ የሚያያቸውን በቆሎ ሻጮች ጠጋ ብሎ "በቆሎ ስንት ነው?" ብሎ ከጠየቃቸው በኋላ፣ በምላሻቸው ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ማለፉ የሚገርም አይሆንም።

 

ሳሪስ አካባቢ ጠዋት ላይ የሚደረገው የበቆሎ ገበያ በአይሱዙ መኪና በመሆኑ የመወደዱን ምክንያት ለማወቅ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ የዛሬ ዓመት በዚህ የበቆሎ እሸት መድረሻ ጊዜ፣ ቢያንስ በቀን 30 አይሱዙ በቆሎ ይገባ ነበር፤ እንደ ነጋዴዎቹ ገለፃ፣ አሁን ሳሪስ ላይ በሦስት ቀን አንድ አይሱዙ፣ መርካቶ ደግሞ በቀን እስከ ሦስት አይሱዙ ከደቡብ ክልል በተለይ ከሻሸመኔ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

 

እጥረቱ ከተከሰተ በኋላ አከፋፋዮች በማዳበሪያ ማከፋፈል ትተው፣ በቁጥር ማከፋፈል መጀመራቸው እና ሲያከፋፍሉም አንድ በቆሎ አንድ ብር ከ50 ሣንቲም ይሸጡና ተመርጦ ከስር የቀረው ዲቃላ በቆሎ በአንድ ብር ከ 20 ሣንቲም ይሸጣል።

 

ወደሚከፋፈልበት ቦታ ዘግይተው የሚደርሱ ሻጮች፣ ባዶ እጃቸውን እንደሚመለሱ የገለፁት ነጋዴዎች፣ ፍላጎቱና አቅርቦቱ ፈጽሞ እንደማይመጣጠን ይናገራሉ።

 

አምና ይኼን ጊዜ የክረምቱን ዝናብና ብርድ፣ በሁለት ብር ስድስት በቆሎ ገዝቶ፣ ክረምቱን ወጥቶ ለዘንድሮው ክረምት የደረሰው የኀብረተሰብ ክፍል፣ ያለፈውን ዓመት የበቆሎ ግዢ ታሪክ መድገም ከፈለገ፣ ለስድስት በቆሎ 12 የኢትዮጵያ ብር እንደሚያስፈልገው ካጣራነው የበቆሎ ገበያ ማወቅ ችለናል፡፡

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ