ሠላሳ ነጋዴዎች ታሰሩ

Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. March 07,2008)፦ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና የአላቂና የጥቃቅን እቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ንረት እያሳዩ ከመሆዩም በላይ ትላንትና አንድ ብር ከሃያ አምስት ይሸጥ የነበረ የአንድ ኪሎ ጨው ዋጋ እንደየአካባቢው የሽያጭ ዋጋ ከ7 ብር እስከ 12 ብር እየተሸጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ምንጮች ገለጹ።

 

ምንጮቻችን እንደገለጹት ዛሬ ሠላሳ የጨው ነጋዴዎች ዋጋ እንዲጨመር አድርጋችኋል በሚል የታሰሩ ሲሆን፣ በጥቃቅን አላቂ እቃዎች ላይ የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ሁለት ብር ከሃምሳ ይሸጥ የነበረ የአንድ ሳሙና ዋጋ አምስትና ስድስት ብር፣ በአንድ አነስተኛ ቤት የአንድ ማኪያቶ ዋጋ አራት ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ በነዳጅ፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ የእህል አይነቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ከአንድ ዜጋ የነፍስወከፍ ገቢ ጋር በፍጹም የማይገናኝ መሆኑን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።

 

የዋጋ ንረቱን አሳሳቢነት በሚመለከት ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚ ምሁር እንደገለጹት "በጨው ላይ ብቻ በዛሬው ዕለት የታየው የዋጋ ጭማሪ ከ460% እስከ 860% እንደየአካባቢው ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን፣ ይህ መንግሥት የሀገሪቱ ዋልታ የሆነውን የኢኮኖሚ ይዞታ መቆጣጠር የተሳነው መሆኑን በግልጽ ያሳያል" ካሉ በኋላ "ይህንን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት ነጋዴዎችን ማሰር መፍትሄ እንደማይሆንና አገዛዙ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባዋል" ብለዋል።

 

አክለውም "ይህ ካልሆነና የኢኮኖሚው ይዞታው በካድሬዎች ብቻ የሚመራ ከሆነ የሃገሪቱ የገንዘብ አቅም እየተሽመደመደ አሁን ካለበት በእጥፍ ሊያሽቆለቁል ይችላል" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ