ነጋዴው በጠባቂ መንቀሳቀስ ጀምሯል  

 ብር ከ25 የነበረው አንድ ነጠላ ሻማ ስድስት ብር ገባ  

የመሣሪያ ሽያጭ ተበራክቷል

Ethiopia Zare(ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2000 ዓ.ም. May 28, 2008)፦ በተለይ በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞችና የገጠር ከተሞች አካባቢ ዕለት በዕለት የሚታየው የትናንሽና አስፈላጊ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ ነዋሪዎችንና ነጋዴዎችን እያራራቀ መሆኑን ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ ጠቆመ። እንደ መረጃው አገላለጽ በመላ ሀገሪቱ የሚታየው የገበያ ዋጋ ጭማሪ በየዕለቱ የሚያድግ ከመሆኑ የተነሳ ነዋሪው ማኅበረሰብ ሊቋቋመው ከማይችለው አዘቅት ውስጥ እየገባ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

 

በአጭር ጊዜ እንኳን ከፋሲካ በዓል በፊትና በኋላ ባለ የገበያ ንጽጽር ከ90% እስከ 300% የጨመረ ሲሆን፣ አላቂ በሚባሉና በየዕለቱ አስፈላጊ በሚባሉ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረቱ እጅግ እያየለ መጥቷል። በምግብ ነክ አንድ እንቁላል አንድ ብር ሲሆን፣ ሽንኩርት ኪሎው 3 ብር፣ ካሮት ኪሎ 6 ብር፣ ቲማቲም ኪሎው 4 ብር፣ ድንች ኪሎው 6 ብር፣ ጤፍ ኩንታሉ ከ850 እስከ 1000 የኢትዮጵያ ብር ሲሆን፤ የለስላሳ መጠቶች እስከ 4 ብር በመደበኛ ምግብ ቤቶች ይሸጣል። ጤፍ በአንዳንድ ቦታዎችም ነጭ ጤፍ ኩንታሉ እስከ 1300 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል። ብር ከሃያ አምስት ሣንቲም የነበረው የአንድ ነጠላ ሻማ ዋጋ እስከ 6 ብር የደረሰ መሆኑንና ቤንዚን ሊትሩ 10 ብር፣ 15 ሊትር ጋዝ 99 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ 170 ብር ገብቶ በጣም ተወደደ ሲባል የነበረው የሲሊንደር ጋዝ ማስሞያ ዋጋ 300 ብር መግባቱን የተማረሩ ገበያተኞች ገልጸውልናል።

 

የመብራት በፈረቃ መሆኑን ተከትሎ  በሀገር ውስጥ የሚመረተውና አንዱ ፓኬት ስምንት ነጫጭና ቀጫጭን ሻማዎችን የሚይዘው ሻማ፤ አሁን በቅርቡ ፓኬቱ አስር ብር (በነጠላ ብር ከሃያ አምስት ሣንቲም) የነበረ ሲሆን፣ በክፍለሀገሮች ፓኬቱ እስከ 48 ብር (በነጠላ ስድስት ብር) ሲሸጥ፤ በአዲስ አበባ ደግሞ 32ብር (በነጠላ አራት ብር) ሆኗል።

 

በአንዳንድ ከተሞች በተለይ በባህርዳር፣ በደሴ፣ በናዝሬት፣ ድሬዳዋና በጂማ አካባቢ በመደወል ያለውን የገበያ ንረት በሚመለከት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም የምሬት አስተያየታቸውን የሰጡን ሲሆን፣ በተለይ አንዲት ግለሰብ ‘አንዲት ሴት ልጄ ዐረብ ሀገር ስለምትኖርና ሁለት የቀሩ ልጆቼን ብቸኛ እናት ሆኘ የማሳድግ በመሆኔ በስጋት ነው የምኖረው፤ በዚህ ኑሮ ያስመርረኛል በሌላ በኩል ደግሞ ልጇ ውጭ ሀገር ትኖራለችና ገንዘብ ይኖራታል ብሎ አንዱ እንዳይገለኝ እሰጋለሁ’ በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

 

ሌላ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ግለሰብም ‘ራሴንና ቤተሰቤን ለመጠበቅ ሽጉጥ መግዛት የግድ ይለኛል’ ብለዋል። ከዚሁ የገበያ ንረት ጋር በተያያዘም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመሣሪያ ሽያጭ እየተበራከተ ከመሆኑም በላይ በውስጥ ለውስጥ ሽያጭም የመሣሪያ ሽያጩ ዋጋ እጅግ እየተወደደ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል።

 

በነጋዴው ማኅበረሰብ አካካቢም ከፍተኛ ስጋት ያለ ከመኖሩም በላይ ነጋዴዎች ከንግድ ቦታቸው ወደቤታቸው ለመመለስ ሁለት ወይንም ሦስት ወጣቶችን ከገጠር አስመጥተውም ሆነ በራሳቸው ወይንም በጎረቤት ልጆች ታጅበው መሄድ ግዴታ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል።

 

ይህንኑ የገበያ ዋጋ ንረትን በሚመለከት ያነጋገርናቸው ባለሙያ እንደሚሉት "ሁኔታው በሌሎች ሀገሮችም እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን ያህል ቅጥ ያጣና ስርዓት የጎደለው የገበያ እንቅስቃሴና ውድነት የትም ቦታ ያልታየ ነው" ካሉ በኋላ፤ "በሀገራችን እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት የሀገሪቱን የፖለቲካና የማኅበራዊ ሕይወት አቅጣጫ በእጅጉ ሊያዛባ ከመቻሉም በላይ የአምባገነን አገዛዞች መጥፊያ መጀመሪያው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መዋዠቅ፣ ብሎም ማሽቆልቆል ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ