በስቶክሆልም የሚደረገው 6ኛው የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ዛሬ ተከፈተ
በዮናታን ፀጋዬ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. July 31, 2008)፦ ስድስተኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ዛሬ ማምሻውን በ18፡30 ሰዓት ላይ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም “ኦሽታ” በተሰኘው ክፍለ ከተማ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ”ቁጭት” በተሰኘው ፊልም በይፋ ተከፈተ።
ስቶክሆልም በጋው ከገባ ጊዜ ጀምሮ በዛሬው ዕለት ጠንከር ያለ ሙቀት የነበራት ሲሆን፣ በአማካኝ ወደ 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበር። ኦሽታ የሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጥቅጥቅ ብሎ ሞልቶ መቀመጫዎቹ ሁሉ ተይዘው ነበር። ቆመው የመክፈቻ ሥነስርዓቱን የታደሙትም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ሙቀቱ ኃይለኛ ስለነበር በርካታ ታዳሚዎች በያዙት ወረቀት ፊታቸውንና ሰውነታቸውን ለማቀዝቀዝ ያራግቡ ነበር።
በስዊድን የኢትዮጵያ ስፖርትና የባህል ፌስቲቫሉ አዘጋጅ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ደመቀ የ”እንኳን ደህና መጣችሁ!” ንግግር በማድረግ በአዳራሹ ለተገኙት ከ450 እስከ 500 ለሚገሙቱና ከተለያዩ አውሮጳ ሀገራት ለመጡት የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች የፌስቲቫሉን መከፈት አብስሯል። አቶ መኮንን በዚሁ ንግግሩ ፌስቲቫሉ የሠላምና የፍቅር ይሆን ዘንድ በአዘጋጅ ኮሚቴው ስም ያለውን መልካም ምኞት ገልጿል።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት የሚገኙት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ በተለይም 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት መንግሥቱ ወርቁ እና ሉቺያኖ ቫሳሎ መሆናቸውን አቶ መኮንን ተናግሯል። ሉቺያኖ በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንበል የነበረና 2ኛውን ግብ ማግባቱ አይዘነጋም።
አቶ መኮንን በነገውና በተነገወዲየው የሚኖረውን ዝግጅት በአጭሩ አስተዋውቋል። የመዝጊያው ሥነስርዓት ላይ አራት ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን ይገኛሉ። እነሱም አቦነሽ አዳነ፣ ሕብስት ጥሩነህ፣ ገነነ ኃይሌ እና ሻምበል በላይነህ ሲሆኑ፤ በስዊድን ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን በአንድ መድረክ ላይ መገኘታቸው መሆኑ ታውቋል።
ይህንን የመዝጊያ ዝግጅት አስመልክቶ አቶ መኮንን ከሁለት ሺህ ሰው በላይ የሚያስተናግድ ዳስ ቴንስታ በተሰኘው ክፍለከተማ እንደሚዘጋጅና ከ22፡00 ሰዓት ጀምሮ ለታዳሚው ክፍት እንደሚሆን ገልጿል።
ከአቶ መኮንን በመቀጠል የ”ቁጭት” የተሰኘው ፊልም አዘጋጅ (ዳይሬክተር) አቶ ዮሐንስ ተረፈ ስለፊልሙ አጭር ማብራሪያ ሰጥቶ ፊልሙ ለታዳሚው መታየት ጀመረ። ቁጭት የተሰኘው ፊልም የሚያጠነጥነው በተለይ በኢትዮጵያውያን የስደት ኑሮ ላይና በቤተሰብ ዙሪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ውስጥ የተሠራ ነው። ፊልሙ የቤተሰብ ድራማ፣ ትምህርት ሰጪና አዝናኝ ነው።
”ቁጭት” ሎንዶን ላይ ሴፕቴምበር 9, 2007 እንደተመረቀ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ኖቨምበር 14, 2007 ለመጀመሪያ ጊዜ መታየቱንና ስዊድን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ለዕይታ መቅረቡን የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልጿል። አቶ ዮሐንስ አክሎም በአውሮጳ በጀርመን ፍራንክፈርት መታየቱን ገልጾ በአራት የአሜሪካን ስቴቶች ለህዝብ ዕይታ መቅረቡንና ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰባት ወራት በሲኒማ ቤት እንደነበር ገልጾልናል። በቅርቡም በዲቪዲ ለገበያ እንደሚቀርብ ሳይገልጽ አላለፈም።
በቁጭት ላይ ከተሳተፉት ተዋንያን ውስጥ ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ የሆኑት የጀግናው የአብዲሳ አጋ ልጅ እጅጋየሁ አብዲሳ፣ ጀንበሬ አሰፋ፣ ሜሮን ተሾመ፣ ነዋሪነታቸው እንግሊዝ ከሆኑት ውስጥ ደግሞ አናኒያ አበበ፣ ሐና ፀጋዬ እና ዳዊት ገሠሠ ጥቂቶቹ ናቸው። የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ነዋሪነቱ እንግሊዝ የሆነው አቶ አለማየሁ ጨመዳ፣ ደራሲው ደግሞ መስፍን ግርማ ናቸው። የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ተረፈ ነዋሪነታቸው ሎንደን፣ እንግሊዝ ነው።



