7ኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርት ውድድር በፓሪስ

ምሥጢረ ኃይለሥላሴ

ላለፉት አምስት ዓመታት በአውሮፓ የኢትዮጵያውያንን የእግር ኳስ ውድድር ተከታትያለሁ። ለEthiosports.comም ሪፖርቶችን፣ ዘገባዎችን ከግምገማ ጋር አቅርቤያለሁ። በአብዛኛው ብዙም ያልተቀየረ ቢሆንም የተመልካች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ መታየቱ ለዕድገቱ መለኪያ ነው ከተባለ ዕድገት አሳይቷል ማለትም ይቻላል። በየዓመቱ ጉድለቶችን የምንጠቁመው በሚቀጥለው እንዳይደገም ለማድረግ ቢሆንም አልሰመረልንም። ዕድገት ታይቷል ሲባል ያልተፈለገውና እንዲታረም የተፈለገውም በዚያው መልኩ አድጓል ማለት ሊሆን ነው።

 

ዋናው የጊዜ ነገር ነው። ለየአንዳንዱ ግጥሚያ የተመደበው 20 + 20 = 40 ደቂቃ ሆኖ ጨዋታው እስኪጀመር ድረስ ቢያንስ ለሰዓታት መጠበቅ የግድ ነው። የሚዘገየው በደቂቃዎች ወይም በሰዓታት ሳይሆን ዘግይቶ ዘግይቶ ያደረም ግጥሚያ አይተናል። እንዲያውም ለምንስ የጊዜ ሰሌዳ አስፈለገ? እገሌ ከእገሌ ጧት ረፋዱ ላይ ሌሎቹ ደግሞ ጥላ በረድ ሲል ይጫወታሉ ቢባል ይበቃ አልነበረም ወይ? ሲባልም ሰምተናል። በዚህ በኩል የታየው መሻሻል በተቃራኒው 20 እና 30 ደቂቃ መዘግየት በእጥፍ ድርብ መጨመሩ ነው።

 

ብዙውን ጊዜ የዝግጅት ቦታዎቹ ከከተማ ራቅ ያሉ ስለሚሆኑ እንግዶች ከዚያው ቦታ ሳይርቁ ማግኘት የሚፈልጉትን ምግብም ሆነ መጠጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አለመቻላቸው፣ ከዚያው ከእንጀራ ሌላ ለሕጻናት የሚሆኑ ምግቦች አለማግኘት ትልቁ ችግር መሆኑን ስናስታውስ የዘንድሮው የፓሪሱ ዝግጅት በዚህ ረገድ መሻሻል ማሳየቱን ሁሉም ያየው በመሆኑ ብዙ የሚያከራክር አይመስለኝም። መጠጡም ቢሆን ከዚያ በረከሰ ዋጋ ለኪሳራ ሊዳርግ ካልሆነ በስተቀር ተወደደ የሚባል አልነበረም። ለምሳሌ አንድ ጣሳ (3.3) ሃይኒከን ቢራ በ1.50 ዩሮ ወደመጨረሻው ላይ በ1.00 ዩሮ ሲሸጥ አይተናል፤ ገዝተናልም። የሚወቀሱበት ሳይጠፋ “ሕጋዊ ዘረፋ” ማለቱ የሚያስተዛዝብ ግምገማ ይሆናል። በኳሱ ዙሪያ እንቆይና አንዳንድ ያልተሟሉ ክለቦች ተስተውለዋል። እነሱም ቢሆኑ “አዲሶች” ከሚባሉት ሳይሆን ከነባሮቹ መካከል በመሆናቸው ለሚቀጥለው ዓመት እንዲጠናከሩ በምክርም ሆነ በሚቻለው ሁሉ ለመርዳት መሞከር እንጂ ዓይናችሁ ላፈር ባይባሉ መልካም ይመስለኛል።

 

በኮሎኙ ውድድር ወቅት የሴቶች የመረብ ኳስም ተጀምሮ እንደነበር እናሰታውሳለን። ዛሬ ስሙም አይነሳ - ለምን? የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ከሁለት ዓመታት በፊት ሆላንድ ላይ በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀቱን ስናስታውስ። ባለፈው ዓመት ስቶክሆልም/ስዊድንም ኳሱ የሩጫ ውድድርም መደረጉን ያልዘነጋን የዘንድሮው የተሻለ ይሆናል ብለን ጠብቀን ስላልሆነ አዝነን ተመልሰናል። በተለይም በኢትዮጵያችን ውስጥ በእግር ኳሱ ዙሪያ የተፈጠረው ቀውስ ውጪ በሚያድጉ ወጣቶች ካልተደጎመ በቀላሉ አያንሰራራም የሚል መልዕክት መተላለፉን የሰማን ሁሉ በናፍቆት የጠበቅነው የወጣቶች ውድድር አሳዛኝም ተስፋ አስቆራጭም ነበር ማለቱ ማጋነን አይሆንም።

 

የስዊስ ቡድን ዕድሜያቸው ከ6-12 የሆኑ ልጆች ማሰለፍ እየቻለ 12 ዓመት የሆናቸው ትልልቆች ናቸው ተብለው ከሜዳ ከተወገዱ በኋላ የአራትና አምስት ዓመታት ሕጻናትን አንድ ኳስ ተከትለው እንዲሯሯጡ ማድረጉ ፍጹም ያልታሰበበትና ደካማ ዝግጅት ለመሆኑ አይነተኛ ማስረጃ ነው። ሩቅ ሳንሄድ ብዙ ግብ የተቆጠረባቸው ክለቦች የችግራቸው መንስዔ ተተኪ ወጣቶች አለማዘጋጀታቸውና የዛሬ 7 እና 8 ዓመታት በተጫወቱት ተጨዋቾች ውጤት ለማግኘት መሞከራቸው አይደለምን? በአጭሩ የወጣቶች ውድድር የተሻለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እላለሁ።

 

ዋናው ያሰባሰበን ኳሱ ሆኖ በዚያ ዙሪያ ሌሎች ተግባራትም በዝግጅቱ ላይ ተጽዕኖ በማያሳድር መልኩ ቢከናወኑ ተቃውሞ ሊገጥማቸው አይገባምና ተከናውነዋል። የሀገር ልብስ፣ የሙዚቃ ሲዲዎች፣ የፎቶ ሥራዎችን ለገበያ ለማቅረብ ቦታ በውድ የተከራዩ እያሉ እነዚያ ደጃፍ ላይ የጉልት ሥራ ሲሠራ ተከራዩም ገበያውን ስለሚያውከው አዘጋጆቹም ደንባቸው በመጣሱ ተቃውሞ ቢያሰሙ ማጉረምረሙ ዓይን አውጣነት እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም። ምናልባትም በየመስኩ (የፖለቲካ ቡድኑ የፖለቲካ ሲምፖዝየም፣ የጫት ነጋዴው የጫት ቃሚዎችና አቃቃሚዎች ጉባዔ በማዘጋጀትና በመጋበዝ) የዚያን አይነት ህዝብ የሚያሰባስብ ዝግጅት አዘጋጅቶ መሞከር ነው እንጂ፤ በባዶ ሜዳ በሰው ድግስ ካላዘዝኩ ብሎ ቡራ ከረዩ ያስተዛዝባል።

 

የጫት ነገር ከተነሳ አይቀር በየዓመቱ ተሻሽሎና አድጎ ብዙ ታዳሚም አፍርቶ ያየነው የጫት ጉዳይ ነው። ፌደሬሽኑ ከአዘጋጅ ቡድን ጋር በመተባበር እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። በዓሉ የቤተሰብ በዓል ነው እያልን ያንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጊት ለማሳየት ልጆች ተይዞ የሚኬድበት ቦታ አያደርገውም። ዛሬ እነአቶ መለስ ዜናዊ በቀጥታ ጫቱ ንግድ ላይ ገብተውበታል። ለሸዋ ልጆች ጫት በገፍ በየአይነቱ ሲቀርብላቸው፤ ትግራይ ውስጥ ግን ሕገ-ወጥ ሆኗል እየተባልን ባለንበት ወቅት፤ ስደት ድረስ ሲልኩልንና በገንዘባችን ጤናችንን ሲያናጉት “እምቢ!” ማለት መቻል ነበረብን። ሊታሰብበት ብቻ ሳይሆን እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነውና ዛሬ ነገ ሳይባል መታረም ይኖርበታል። በዚህ ቅር የሚለውም ካለ መቼስ ምን ይደረጋል መቀጠል ግን የለበትም። አደገኛ ነውና።

 

ውይ የኔ ነገር ሌላ ሌላውን እያነሳሳሁ ኳሱን ተውኩት። አዎ! ኳሱ … ባለፉት ሁለት ዝግጅቶች ድንቅ ጨዋነትና ጨዋታ በማሳየት የተደነቀው የስዊሱ ቡድን ዘንድሮ በሁሉም መልኩ (የፀባይ ዋንጫውን በይሉኝታ ባይነፍጉት) ባለ ድል ሆኖ ተመልሷል። ኮከብ ግብ ጠባቂ የስዊሱ ጎሹ፣ ኮከብ ተጨዋች የስዊሱ ሰይፈ፣ ኮከብ አሰልጣኝ የስዊሱ አ.ሥላሴ ሽልማት ስላልተዘጋጀ እንጂ ኮከብ ደጋፊዎችም ስዊሶቹ እንደነበሩ ሁሉም የተስማማበት ሐቅ ነው። በደጋፊ ብዛትም ስዊሶች የሚስተካከላቸው ቀርቶ የሚቃረባቸውም አልነበረ። ቡድናቸው በተጫወተባቸው ሜዳዎች ሁሉ እየተከተሉ የሚያሰሙት ድጋፍ፣ ተፎካካሪን መዝላፍ ሳይሆን የራስን በማሞገስ ማበረታታት ተፎካካሪም ጥሩ ሲጫወት እንደዚሁ አድናቆትን በጭብጨባ መግለጽን የመሳሰሉ የበሰለ የኳስ ጨዋታ ተመልካች ሥነ-ምግባራት ተንጸባርቀዋል።

 

ስዊሶችን እንኳን ደስ ያላችሁ! … ወደ ቅዳሜ ምሽቱ ላምራ።

 

እንደተለመደው በዓሉ የሚዘጋጀው በሙዚቃ ምሽት ነውና የዚህ ዓመቱ የፓሪሱ ዝግጅትም የተለየ አልነበረም። ተጋባዥ ድምፃውያን ጎሣዬ ተስፋዬ እና ብርሃኑ ተዘራ ከአዲስ አበባ የመግቢያ ዋጋ 30 ዩሮ ቦታ አብዛኛዎቹ እንግዶች ካረፉበት ሆቴሎች ትይዩ መንገዱን ሻገር ብሎ በመሆኑ ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ አመቺነቱ ገና ፕሮግራሙ ሲታይ ያስታውቅ ነበርና ባለፉት የነበሩትን ጉድለቶች ሁሉ የሚያካክስ ሊሆን ነው ያሉም አልታጡ።

 

ቀደም ብለን ከእኩለ ሌሊት በፊት ለገባነው ግፊያም አላገኘን። ቦታው በጣም ሰፊ በመሆኑ ለምን እንደተሠራ እንኳን ለመገመት ያዳግታል። ዛኒጋባ ነገር ሆኖ ግማሽ ጣራው ክፍት ነው። ከግዙፍነቱ የተነሳ ሰዉ ወደ ዳንስ ወለሉ (ባለጣራው ክልል) ከተጠጋጋ ጠብ ጠብ ማለት የጀመረው ካፍያ እንደማያሰጋን ተማምነን ጉምጉምታው እጅግም አላስፈራን። የሰዉን ቁጥር ለመገመት ያዳግታል ከ2000 -3500 የሚሉም ነበሩ፤ ብቻ በጣም ብዙ ሰው ተገኝቷል። ለዚያ ሁሉ ሰው አንድ ባር (የመጠጥ)፣ አንድ የምግብ መቀባበያ ብቻ በመደረጉ ብዙ ሰው ተጉላልቷል። ተጠምቶ መጥቶ ተጠምቶ የሄደ እንዳለ የማይታበል መራራ ሐቅ ነው። አስተናጋጆቹ ያን ያህል ሰው አልጠበቁም ነበር? ካለፉት ዝግጅቶች ምን ተምረዋል? ወደ ኋላ ላይ በሩ አካባቢ ድብልቅልቁ ወጥቶ እንደነበር ሰምተናል። አስተናባሪዎች ሳይቀሩ መታወቂያ ባለመዘጋጀቱ በሩ ላይ የቆሙት የውጭ ሀገር ሰዎች ካልከፈላችሁ አናስገባም እንዳሏቸውም ተሰምቷል። እነዚህ እነዚህ የዝግጅት ድክመቶች ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ።

 

ይህ በዚህ እንዳለ አዳራሹ ውስጥ የዘፋኞቹ (ይቅርታ አርቲስት በሉን ብለዋል ለካ!) ዱካ አልሰማ አለ! በፈረንጆቹ ሰዓት አቆጣጠር 11:30 (ከምሽቱ አምስት ተኩል) ገደማ ለጤና አደገኛ በሆነ ኃይል ሲያምባርቅ የቆየው የሙዚቃ መሣሪያ መቆራረጥ ጀመረ። እንዲያ እንዲያ እያልን እስከ 7:25 ተቆየና ሁለቱም በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አጊጠው ብቅ ሲሉ መቼም ውሻ ሆዶች ነንና በጭብጨባ ተቀበልናቸው። በፈረቃ ሁለት ሁለት ይዘፍኑና ዲጄው ቦታ ይይዛል። “ማረፋቸው ነው። መንገዱ አድክሟቸው ይሆን?” አሉ አንድ አጠገባችን የነበሩ እናት። “ምነው ሻምበል በላይነህን ቢጋብዙት” አለ ሌላው የተናደደ የሚመስል ወጣት።

 

እኔ በግሌ ሁለቱንም በሀገር ወዳድነታቸው፣ በችሎታቸው የማደንቃቸውና የምወዳቸው ቢሆንም ያ ቅዳሜ ምሽት ተቀልዶብናል ከሚሉት ወገን የምደመር ነኝ። በቃ ሰንደቅ ዓላማችንን ካዩ ምንም አይሉ ብለው ነው?

 

በየዓመቱ መታረም አለባቸው የምንላቸውን ነጥቦች በእውነተኛ የሀገርና የስፖርት ፍቅር ስሜት አስተላልፈናል። ፌደሬሽኑም ሆነ አዘጋጆቹ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ይመስላል። ለዚህም ነው የሚያስወቅሳቸው በቂ ነገር እያለ ሌላ ኃጢአት አንለጥፋባቸው የምንለው።

 

ዝግጅቱ ወደድንም ጠላንም በዚያ ፌደሬሽን አነሳሽነትና የበላይነት በየዓመቱ ያገናኘናል። እነሱም ደንብ አላቸው። እነሱ በሚያዘጋጇቸው ቦታዎች ሁሉ ለድርጅትም ሆነ ግለሰብ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የምንፈልግ ሁሉ ደንባቸውን ማክበር ይጠበቅብናል። በመጨረሻም ስፖርት ለፍቅር፣ ስፖርት ለጤንነት፣ ስፖርት ለአንድነት ነውና ሌላ ትርጉም አንስጠው። የዛሬ ዓመት አምስተርዳም በሠላም ያገናኘን!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ