Teddy Afroምክንያቱ የቴዲ ጠበቃ ለአዲስ ነገር ጋዜጣ ዳኛውንና ተርጓሚውን እንደሚከስ መግለጹ ነው

Ethiopia Zare (ሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. August 04, 2008)፦ የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ የቴዲን ጉዳይ የሚያዩትን ዳኛ ልዑል ገብረማርያምን እና የምንሊክ ሆስፒታል አስተርጓሚን እንደሚከስ ለአዲስ ነገር ጋዜጣ በመግለጹና ጋዜጣው ዜናውን በመዘገቡ ምክንያት የጋዜጣው ዋና አዘጋጆችንና ጠበቃውን ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርባቸው ዳኛው በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት የጋዜጣው አዘጋጆች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ገለጸ።

 

 

የአዲስ ዜና ዋና አዘጋጅ ካለ አዘጋጁ፣ ከሌለ ደግሞ ምክትል አዘጋጁ ይቅረቡ ተብሎ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲደርሰው፣ ዛሬ ጠዋት ፖሊሶች ዋና አዘጋጁን አቶ መስፍን ነጋሽንና ም/ዋና አዘጋጁን ግርማ ተስፋውን አስሮ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸዋል። ከዚያም ፖሊሶቹ ቃላቸውን ተቀብለው ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት አቀርቧቸዋል።

 

 

አዘጋጆቹ የቀረቡት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ዳኛው የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚያዩት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ነበሩ። ዳኛው ጥያቄዎችን አቅርበው ከአዘጋጆቹ ምላሽ ካገኙ በኋላ ምክትል ዋና አዘጋጁን ወዲያውኑ እንዲለቀቅና ዋና አዘጋጁ ለነገ ጠዋት 5 ሰዓት በድጋሚ ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ለዛሬ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲያድር የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በዚህም መሰረት ምክትል ዋና አዘጋጁ ሲለቀቅ ዋና አዘጋጁ ግን ታስሯል።

 

 

ዳኛ ልዑል የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ዛሬ ማምሻውን ተፈልጎ ይቅረብ በተባለው መሰረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ግን ሳይቀርብ ቀርቷል። እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ነገ ጠበቃው ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል።

 

 

ጠበቃው ”የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚከታተለው ዳኛ የመከራከር መብቴን ተጋፍቷአል፣ ...” በማለቱ የዳኝነት ነፃነትን ተጋፍቷል በሚል፣ ጋዜጣው ደግሞ የዳኝነት ነፃነት የሚጋፋ ዘገባ ሰርቷል በሚል ነው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገው። እስካሁን ከሳሻቸው ማን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ