የቴዲ ጠበቃና የአዲስ ነገር አዘጋጅ ለነገ ተቀጠሩ
ታስረው ይቆዩ ተብሏል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም. August 05, 2008)፦ በዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ትዕዛዝ ዛሬ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የታዘዙት የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋና የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ ታስረው ካደሩበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው፤ ለነገ መቀጠራቸውን የፍርዱን ሂደት ከተከታተሉ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ለማወቅ ችለናል።
ለጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ጠበቃ ሆነው የተከራከሩት ጠበቃ አበበ አሳምን ደንበኛቸው ብይኑን አስመልክቶ ይግባኝ መጠየቅና ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ክስ ማቅረብ መብታቸው መሆኑን ገልጸዋል። "ዳኛው የዓቃቤ ሕጉን ሥራ ተክቶ ሠርቷል" የሚለውን አስተያየት መስጠትስ የሕግ አግባብ አለው ወይ? ብለው የጠየቁ ሲሆን፣ የአቶ ሚሊዮን አሰፋ ጠበቃ "ይሄ ንግግር ከስሜታዊነት የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ ፍርድ ቤቱ በቅን ልቦና ተመልክቶ ደንበኛዬ በነፃ ያሰናብትልኝ" ሲል ጠይቋል።
ጠበቃ ሚሊዮንም በበኩሉ "ለዳኞች ኮሚቴ የምከሰው አንደኛው ኮንቴንት ወይንም የምከስበት ምክንያት ይሄው ነው። ክስ ማቅረብ መብቴም ነው።" ሲል አቤቱታውን አሰምቷል። ዳኛ ልዑልም "መዝገቡ ተመርምሮ በነገው ዕለት ውሳኔ ይሰጥበታል፤ እስከዛው እስረኞቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስረው ይደሩ" በማለት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በተያያዘም ጋዜጠኛ መስፍን በሕመም ላይ በመሆኑ በዋስ ይለቀቅ ዘንድ ቢጠይቅም ዳኛ ልዑል "የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መድኃኒት ካለው ይተባበርህ" ሲሉ ለነገ እንዲቀርቡ ትዕዛዛቸውን ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱ የዓመቱን የሥራ ጊዜ ነገ ሐምሌ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ጨርሶ ከተነገ ወዲያ ኀሙስ ነኀሴ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ወራት ይዘጋል።