የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ተፈታ፣ ቴዲ ከጨለማ ቤት ወጣ
Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. August 08, 2008)፦ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ”ችሎት በመዳፈር” በሚል ለአንድ ወር ከሃያ ቀናት ከተፈረደበት በኋላ በጠቃው አቶ አበባ አሳምን አማካኝነት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ይግባኝ በማለቱ አቶ ሚሊዮን ዛሬ ማምሻውን መፈታቱን እንዲሁም ቴዲ አፍሮ ደግሞ 27 ቀናት ታስሮ ከነበረበት ጨለማ ቤት እንዲወጣ መደረጉን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጡ።
ፍርድ ቤቶች ነኀሴ 1 ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚዘጉ ቢሆንም አንዳንድ አስቸኳይ ጉዳዮችን የሚያዩ ”ተዘዋዋሪ ችሎት” ተብለው የሚጠሩ ችሎቶች በመኖራቸው፤ የአቶ ሚሊዮን አሰፋ ጠበቃ ደንበኛቸው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ረቡዕ ሐምሌ 30 በጣለው የአንድ ወር ከሃያ ቀናት የእስር ቅጣት ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ዛሬ ጠዋት ይግባኝ ብሎ ነበር።
በዚህም መሰረት ይግባኙን ያየው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተዘዋዋሪ ችሎት ”ጉዳዩ በይግባኝ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ቅጣት ለጊዜው ታግዶ ይቆይ” ሲል ዛሬ ውሳኔ በመስጠቱ የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ዛሬ ማምሻውን ከሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት ከታሰረበት መፈታቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና ቴዲ አፍሮ ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. በዋለው ችሎት "… እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። …" ብሎ በመናገሩ ምክንያት ወደ ጨለማ ቤት መወርወሩንና የልደት በዓሉን ትላንት በጨለማ ቤት ማክበሩን መዘገባችን አይዘነጋም። ቴዲ አፍሮ በዛሬው ዕለት ለብቻው አንድ ክፍል ውስጥ ታስሮ ከነበረበት ጨለማ ቤት ወጥቶ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዲታሰር መደረጉን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ከወሕኒ ቤት እስር አስከፊው ቅጣት ቢኖር ለብቻ ጨለማ ቤት መታሰር ሲሆን፣ በእንዲህ ያለ እስር ጊዜ በጨለማ ቤት የታሰረው ሰው ከማንም ሰው ጋር የማይገናኝ በመሆኑና እንደልብ መንቀሳቀስ፣ ሰውነት ማፍታታትና የፀሐይ ብርሃን ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል።



